አፄ ምንሊክ “ውሃ አንጠቀምም” የሚል ስምምነት እንዳልፈረሙ ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ተናገሩ

አፄ ምንሊክ “ውሃ አንጠቀምም” የሚል ስምምነት እንዳልፈረሙ ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ተናገሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ታላቁ ኢትዮጵናዊ ንጉሥ ዳግማዊ አፄ ምንሊክ “ውሃ ለጎረቤታችን አንከለክልም” ሲሉ እንጂ “ውሃ አንጠቀምም”  የሚል ስምምነት አለመፈረማቸውን በአ/አ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህር፣ የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ።

ግብፅ እንደ አውሮጳዊያኑ የዘመን ቀመር 1929 እና 1959 የተፈረመውን የቅኝ ግዛት ስምምነት ማስቀጠል ትፈልጋለች ያሉት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፤ ከዚህ በተጨማሪ ግብፅ  በ19 02 ዳግማዊ አፄ ምንሊክ “ውሃ አንጠቀምም  ብለዋል የሚል የሐሰት ትርክት እያስተጋባች እንደምትገኝም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲ በዳግማዊ አፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት የተጀመረ ቢሆንም አሁን ላይ  ግብፆች በተሳሳተ መንገድ ተርጉመው ለዓለም እያስተዋወቁት እንደሆነም ተደራዳሪው አስረድተዋል።
በጊዜው የተደረገው ስምምነት “ውሃ ለጎረቤታችን አንከለክልም፤ የሚል እንጂ ውሃ አንጠቀምም” የሚል እንዳልነበር ያስታወሱት ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ፤
ይህ በግብፅና በደጋፊዎቿ የሚስተጋባ የተለመደ ማደናገሪያ መሆኑ ስለሚታወቅ ቀሪው ዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ በተሳሳተ መንገድ እየተረዳው አይደለም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ስታደርገው የቆየችውና ወደፊትም የምታካሂደው ድርድር ብሔራዊ ጥቅሟን በማይነካ መንገድ እንደሚሆን ያስረዱት ባለሙያው፤ አሁንም ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚደረገው ድርድር ቀይ መስመሩን አልፎ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ ከሆነ እንደሚቋረጥም ይፋ አድርገዋል።

LEAVE A REPLY