ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ፣ በኢንቨስትመንት ለመሠማራት ፈቃድ ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል 61 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታና ማምረት እንደተሸጋገሩ ተነገረ።

የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መመሪያ፤ በከተማው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ10 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 210 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንደተሰጠ ታውቋል።
ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 11 የጨርቃጨርቅ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የኬሚካልና መሰል አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ መደረጉም ተሰምቷል።
50 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ደግሞ ወደ ግንባታ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፤ ወደ ማምረት የገቡትና በግንባታ ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶችም ለ4 ሺኅ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠራቸው ተረጋግጧል።
ለተገኘው ውጤት በከተማው የተፈጠረው የተረጋጋ ሰላም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር አስተዋፅኦ እንዳደረገው ያመላከተው መረጃ፤ በከተማው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሠማሩ ባለሀብቶች የሚውል 512 ሄክታር መሬት ዝግጁ መሆኑንም ያስረዳል።
በአንጻሩ የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ለረጅም ዓመታት አጥረው ያስቀመጡ ባለሀብቶችን በጥናት በመለየት 57 ባለሀብቶች የወሰዱት መሬት በመንጠቅ ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ እንዲሆን ተደርጓል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም ፤ በቀጣይ ጎንደር የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆና እንድትቀጥል ለማድረግ በዘርፉ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን በጥናት በመመለስ የኢንዱስትሪ ከተማ እንድትሆን በጥብቅ እየተሠራ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

LEAVE A REPLY