አቶ ልደቱ አያሌው ቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አቶ ልደቱ አያሌው ቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢዴፓ አመራር የነበሩትና አርብ እለት አዲስ አበባ ተይዘው ቢሾፍቱ  ከተማ ተወስደው የታሰሩት አቶ ልደቱ አያሌው ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት የታየው አቶ ልደቱ አያሌውን፤ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓመተ ምህረት በቢሾፍቱ ከተማ ለወጣቶች ገንዘብ በመስጠት፣ ለብጥብጥ እና አመፅ በማነሳሳት ወንጀል እንደጠረጠራቸው ፖሊስ ገልጿል።
 ፖሊስ አነጋጋሪውን ፖለቲከኛ በተመለከተ ለፍርድ ቤት በሰጠው አስተያየት፤ ባለፈው አርብ ዐራት ሰዐት ላይ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው እና በዚህም ወቅት ሁለት ሽጉጦች እንደገኘባቸው አስረድቷል።
ይህን ያለው የኦሮሚያ ፖሊስ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ለማቅረብም የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ዛሬ ለተሰየመው የቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል።
 ተጠርጣሪው አቶ ልደቱ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቋሚ አድራሻ እና ቤት ያላቸው፣ መታወቂያቸውም በዚያው መሆኑን ጠቁመው፤ በጊዜያዊነት በቢሾፍቱ ቤት ያላቸው መሆኑን በማመን፣ በፌደራል ፍርድ ቤት ነው መቅረብ ያለብኝ በሚል መቃወሚያ በማንሳት ተከራክረዋል።
 የዛሬ ዓመት የልብ ቀዶ ጥገና አድርገውበት ወደነበረው ሀገር ዛሬ 4 ሰዓት ላይ ለመጓዝ የተዘጋጁ መሆናቸውን፣  ትኬት ቢቆርጡም አሁን ታስረው እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ልደቱ አያሌው፤ የአስም በሽተኛ መሆናቸውን ከመናገራቸው ባሻገር፤ ያለሁበት የእስር ሁኔታ ለኮቪድ-19 እንዳያጋልጠኝ እሰጋለሁና  ይህ  ታሳቢ ተደርጎ የዋስትና መብቴ ይከበርልኝ  ሲሉ ጠይቀዋል።
 ፖሊስ በበኩሉ የተጠርጣሪው የእስር አያያዛቸው ምቹ እና ጥንቃቄ ያለው መሆኑን በማስረዳት ፤ ከእስር ቢፈቱ ማስረጃ  ያሸሹብኛል በሚል በዋስ እንዳይወጡ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
 ፍርድ ቤቱ አቶ ልደቱ አያሌው ጉዳያቸው በቢሾፍቱ አይታይም በሚል ላቀረቡት ጥያቄ፣ ወንጀሉ የተፈፀመው በቢሾፍቱ በመሆኑ እና የእርሳቸውም መኖሪያ በዚያው ከመሆኑ አኳያ፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እዚያው የማየት ሥልጣን እንዳለው በማስረዳት በተጀመረው ችሎት መታየት እንዲቀጥል ወስኗል።
በተመሳሳይ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜን ፍርድ ቤቱ መፍቀዱ ታውቋል።

LEAVE A REPLY