የትግራይ ክልል ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን የምዝገባ ጥሪ አቀረበ

የትግራይ ክልል ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን የምዝገባ ጥሪ አቀረበ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ስድስተኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ ያለምርጫ ቦርድ ፍቃድ ህወሓት በወሰነበት በትግራይ ክልል  በሚከናወነው ምርጫ ለመወዳደር የሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲመዘገቡ ጥሪ ቀረበ።

ከአንድ ሳምንት በፊት የተቋቋመው የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ሊካሄድ በታቀደው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ፓርቲዎች ” ኑ ተመዝገቡ” የሚል መልዕክት አስተላልፏል።
ኮሚሽኑ ባቀረበው ጥሪ መሰረት በምርጫው ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶችና የግል ተወዳዳሪዎች ከማክሰኞ ሐምሌ 21/2012 ዓ.ም እስከ ሐሙስ ሐምሌ 23/2012 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ሊመዘገቡ ይችላሉ ተብሏል።
 የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መምህር ሙሉወርቅ ኪዳነ ማርያም
እንደተናገሩት ፤ ኮሚሽኑ በምርጫው መሳተፍ ለሚፈልጉ ወገኖች ቀርበው እንዲመዘገቡ ጥሪ ከማቅረብ ውጪ፣ ለምርጫው አፈጻጸም ስለሚያስፈልጉ የጊዜ ሰሌዳና ሌሎች ወሳኝ ነገሮች እስካሁን ያሳወቀው ነገር የለም።
ምርጫው ይካሄድበታል ተብሎ እየተነገረለት ትክክለኛ ቀንም እስካሁን የተገለጸ ነገር ባይኖርም፤ ምርጫው የሚካሄድበት ቀንን ከሚመዘገቡ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመወያየት እንደሚወሰን መምህር ሙሉወርቅ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ገልጸዋል።
በቅርቡ በህወሓት ምልመላ የተቋቋመው ኮሚሽኑ በክልላዊ ምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎችን ለምዝገባ ከመጥራት ውጪ፣ ለምዝገባ የሚያስፈልጉ ዝርዝር ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ ከመግለፅ የተቆጠበ ይመስላል።

LEAVE A REPLY