ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት መምህራንና ተመራማሪዎች የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማእረግ መስጠቱ ተሰማ።
ዩኒቨርሲቲው በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሮፌሰርነት ማእረግ የሰጠው ለፕሮፌሰር አሰፋ አባሙና እና ለፕሮፌሰር አማን ደቀቦ ሲሆን፤ ሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣቸው ምሁራን በረጅም ጊዜ ማስተማር፣ ጥናትና ምርምሮቻቸውን በዓለም ዐቀፍ ጆርናሎች በማሳተምና በማኅበረሰብ አገልግሎት አበርክቶዎቻቸው እንደሆነ ታውቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ፤ ማዕረግ መሰጠቱ የምሁራንን ተወዳዳሪነት እንደማጨምር ጠቁመው፤ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ጊዜ ከ400 በላይ የዶክትሬት ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሆነና ትምህርቱን በጥራት ለመስጠት ምሁራንን የማብቃት ሥራ እያከናወነ እንደሆነም ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሹመቴ ግዛው፤ አዳማ ዮንቨርስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰጠው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በሌሎች ሥራዎች ሊገለጥ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው የተጀመሩ የሽግግር ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሰው ኃይል ማብቃቱን ማጠናከር እንደሚገባው የተናገሩት የቦርድ ሰብሳቢው፤ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣቸው ምሁራንም የበለጠ ተግተው እንዲሠሩ መክረዋል።