የአረፋ በዓል፤ በእስልምና ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ነው

የአረፋ በዓል፤ በእስልምና ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || 1 ሺኅ 441ኛው የኢድ አል አድሃ ወይም አረፋ በዓል በመላው ሀገሪቱ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እንድሪስ  ሕዝበ ሙስሊሙ ይህን አስቸጋሪ ወቅት በመተዛዘንና ያለውን በማካፈል የአረፋ በዓሉን ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዲያከብር ከቀናት በፊት መልእክት ማስተላለፋቸው አይዘነጋም።
የአረፋን በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ልዩ የሚያደርገው የእርድ ሥነ ሥርዓት ከመከናወኑ ባሻገር፣ ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ የሚበላበት፣ መተዛዘንን፣ አብሮነትንና መረዳዳት የሚታይበት  በዓል መሆኑም ይታወቃል።
የእምነቱ ተከታዮች ከሚያከናውኑት እርድ አንድ ሦስተኛው ለምስኪኖች መስጠት ይገባል ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንድሪስ፤  የዘንድሮ አረፋ በዓል ሀገራችን ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያው ውሃ ሙሌት ያከናወነችበት ወቅት በመሆኑም ተጨማሪ ደስታ መሆኑ ተጨማሪ ደስታን እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።
የአረፋ በዓል አደምና ሐዋ የተገናኙበት ሥፍራ እንደሆነ ያስረዱት ሐጅ ዑመር እድሪስ፤  ይህ  በዓል ከነብዩላህ ኢብራሂምና ከእስማኤል ጀምሮ ሲከበር የነበረ በዓል እንደሆነም አስረድተዋል።
በመላ ኢትዮጵያ የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉን ከማለዳው ጀምሮ በጥሩ ሁኔታ እያከበሩት ሲሆን፤ በዓሉ በልዮ ሁኔታ የሚከበርባቸው የስልጤና የጉራጌ ማኅበረሰብ ተወላጅ የሆኑ ሙስሊሞች ከቀናት በፊት ወደ ትውልድ መንደራቸው ሲጓዙ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ነገ ለመላው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እንኳን ለአረፋ በዓል አደረሳችሁ፣ “ኢድ ሙባረክ” ሲል መልካም ምኞቱን ይገልጻል።

LEAVE A REPLY