ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ የታሠሩት የሁሉም ፖለቲከኞችና የቤተሰቦቻቸው የባንክ አካውንት እንዳይንቀሳቀስ መታገዱ ተሰማ።
የተጠርጣሪዎች ጠበቃ በበኩላቸው የባንክ አካውንቶቹ እንዳይንቀሳቀሱ የተደረገው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው በሚል ተቃውሞ እያቀረቡ ነው።
በተባለው መንገድም ይሁን በውስጣዊ ትእዛዝ የባንክ አካውንታቸው እንዳይንቀሳቀስ ከታገደባቸው ሰዎች መካከል የአቶ ጃዋር መሐመድና ቤተሰባቸው፣ የአቶ በቀለ ገርባ እና የቤተሰባቸው ፣ የጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ እና ባለቤቱ እንደሚገኙበት ቢቢሲ ዘግቧል።
በተመሳሳይ የአቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን ጨምሮ ሐረር ከተማን የጽንፈኛ ብሔርተኞች መናኸሪያ እንዲሆን ከፍተኛ የዘረኝነት ፖለቲካን ሲያራምዱ እንደነበር በተደጋጋሚ የሚነገርለት የአቶ ሐምዛ ቤተሰቦች የባንክ አካውንቶች መታገዱን የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ ምንጮች ነግረውናል።
የአቶ ጃዋር መሐመድ እህት የሆነችው ራዲያ ሲራጅ፤ የእሷን ጨምሮ የአምስት ወንድሞቿ የባንክ አካውንቶች እንዳይንቀሳቀስ መታገዱን ጠቁማ፤ ” የእኔም የአዋሽ እና የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አካውንቶች ናቸው የተዘጉት። ለምን እንደተዘጋ ስንጠይቃቸው እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ ስልክ ተደውሎ ነው ዝጉ የተባልነው” ስትል ለቢቢሲ አስተያየቷን ሰጥታለች።
የኦ ኤም ኤን ጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ ባለቤት የሆነችው ታደለች መርጋ፤ የእርሷ እና የባለቤቷ የቁጠባ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ መደረጉን ያወቀችው ትናንት የቤት ኪራይ ለመክፈል በማሰብ፣ ገንዘብ ለማውጣት ወደ ባንክ ስትሄድ ከባንኩ ሠራተኞች በተነገራት ወቅት መሆኑን ገልጻለች።
የባለቤቷን የቁጠባ ሒሳብንም ስትጠይቅ መታገዱን እንደተናገራት ያመላከተችው ወ/ሮ ታደለች፤ “በአካውንቱ ውስጥ ያለው ጥቂት ገንዘብ ነው ፤ ሠርቼ ያመጣሁት ደሞዜ እንጂ ከየት እናመጣለን?” ስትልም የአዘጋጉ ምክንያት ያልተዋጠላት መሆኑን በጥያቄ መልሳለች።
የአቶ በቀለ ገርባ፣ የአቶ በቀለ ገርባ ባለቤት እና የልጃቸው አካውንት እንዲዘጋ መደረጉን ሰኞ እለት የገለጹት የአቶ በቀለ ባለቤት ወ/ሮ ሃና ረገሳ ፤ አካውንቶቹም እስካሁን ዝግ ሆነው እንደሚገኙም አስታውቀዋል።