ጃል ዳውድ ኢብሳ ከሁለት ቀን የቤት ውስጥ እገታ በኋላ ውጭ ወጥተው መንቀሳቀስ...

ጃል ዳውድ ኢብሳ ከሁለት ቀን የቤት ውስጥ እገታ በኋላ ውጭ ወጥተው መንቀሳቀስ ጀመሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከሐምሌ 10 ቀን ጀምሮ ለደህንነትዎ ጥበቃ ልናደርግ ነው የመጣነው ባሉ ፖሊሶች ከቤት እንዳይወጡ የታዘዙት አቶ ዳውድ ትናትት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቢሮአቸው የኦነግ ጽ/ቤት መሄዳቸውን ገለጹ።

 “በሳምንቱ ሐምሌ 17  ቀን ቤት ውስጥ ያሉትም ወደ ውጪ እንዳይወጡ” የሚል ትእዛዝ በፌደራል ፖሊሶቹ መሰጠቱን ያስታወሱት ጃል ዳውድ ከዚህ ቀን ከሰዐት በኋላ ስልካቸው መዘጋቱና ነገሮች የበለጠ አሳሳቢ መሆናቸውን ይናገራሉ።
“ለጥበቃ የመጣው የፖሊስ ኃይልና ስልኬን የዘጋው አካል ግንኙነት ይኑራቸው አይኑራቸው የማውቀው ነገር የለም” ያሉት አቶ ዳውድ፤ “ሐሙስ ዕለት ከአሁን በኋላ ለደኅንነትህ ጥንቃቄ እያደረክ መንቀሳቀስ ትችላለህ መባላቸውን” ተከትሎ ትናንት (አርብ) ወደ ቢሮአቸው መሄድ መቻላቸውን ለቢቢሲ አስታውቀዋል።
“ስልኬ እንዲቋረጥ መደረጉን የደኅንነት ጉዳይ አድርጌ አልወሰድኩትም። ለሌላ ኦፕሬሽን እንደወሰዱት ነው የተረዳሁት። እነዚህ ሁለቱ ይገናኛሉ ብዬ ማመን ትንሽ ያስቸግረኛል፤ ነገር ግን ሊገናኙም ላይገናኙም ይችላሉ። ማወቅ አልቻልኩም” ያሉት ጃል ዳውድ ኢብሳ፤ እስካሁን ድረስም ስልካቸው እንደተዘጋ አረጋግጠዋል።
“ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና ከድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ በኋላ፤ የሆነ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ማንም የሚረዳው ነገር ነው” የሚሉት የኦነግ ሊቀመንበር ከደህንነት አኳያ ይህን ከግምት በማስገባት እንደሚንቀሳቀሱም ገልጸዋል።
“እንዲህ ያለው ጥቃት በማንም ላይ ሊጋጥም ይችላል፤ ምክንያቱም መንግሥት የሕግ የበላይነትን አስከብራለሁ ብሎ ንፁሃን ዜጎችን ከማሰር ውጪ ለሕዝብ መረጃ አይሰጥም፤ የእነዚህ ሰዎች ገዳዮች እነማን ናቸው? የሚለውን ምርመራ አድርጎ ይፋ አያወጣም። ስለዚህ ይህ በማንም ላይ በየትኛውም ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል ተረድተን ነው የምንንቀሳቀሰው” ሲሉም ለሚታዮት ግድያዎች መንግሥትን ተጠያቂ አድርገዋል።
ሰሞኑን እየተናፈሰ ያለውና እርሳቸው ከሊቀመንበርነት የወረዱት ጉባዔ ስለመካሄዱ የተጠየቁት የግንባሩ መሪ “ሚዲያዎች ነገሮችን በከፍተኛ ሁኔታ እያራገቡ ነው፤ ስለስብሰባው ህጋዊነት የሚያጣራ የሕግ ቁጥጥር ኮሚቴ አለ፤ እርሱ ጉዳዮን መርምሮ የሚሰጠውን ምላሽ ሁላችንም እየጠቀቅን ነው” የሚል ድፍን ያለና ሀቁን ያላሳየ ምላሽ ሰጥተዋል።

LEAVE A REPLY