ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ነገ (እሁድ) ሐምሌ 26 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ራሱን ከኮሮና ቫይረስ እየጠበቀ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ።
ም/ ከንቲባ ታከለ ኡማ ነገ ይተከላል ተብሎ በሚጠበቀው 2 ሚሊየን ችግኝ (በመስተዳደሩ የተገለጸ አኃዝ መሠረት) ዙሪያ ለከተማው ከፍተኛ የሥራ አመራሮች መመሪያ ሰጥተዋል።
ከችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ባሻገር፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በመዲናዋ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ለመከላከል ከጤና ሚኒስቴርና ከከተማዋ ጤና ቢሮ የወጡ መመሪያዎች ጎን ለጎን በትክክል እንዲተገብሩም ከንቲባው አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሊተከል በእቅድ ከተያዘው 7 ሚሊየን ችግኝ መካከል፣ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ የሚሆነው ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎችን በማሳተፍ መተከሉ ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።
“የጋራ ቤታችን የሆነችውን አዲስ አበባን በጋራ እንገንባ” ሲሉም መልእክት ያስተላለፉት ከንቲባ ታከለ ኡማ፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከሚተከሉት ችግኞች መካከል ለምግብነት የሚውሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች በመኖራቸው ለከተማ ግብርና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ገልጸዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በአጭር ጊዜ መጠናቀቁ የችግኝ መትከል ጥቅሙን ከወዲሁ የሚያመላክት በመሆኑ፤ ነገ የከተማዋ ነዋሪዎች በመኖሪያ አካባቢያቸው፣ ለተከላ በተዘጋጁ ሥፍራዎች ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ ከመስተዳደሩ ቀርቧል።