ህወሓት የትግራይ ልዮ ኃይልና ሚሊሻዎችን ያጣመረ ወታደራዊ ትዕይንት አሳየ

ህወሓት የትግራይ ልዮ ኃይልና ሚሊሻዎችን ያጣመረ ወታደራዊ ትዕይንት አሳየ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ለጦርነት እና ለብጥብጥ የቋመጠው ህወሓት በትግራይ አነጋጋሪ የሆኑ ድርጊቶችን መፈጸም ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል።

ከፌደራል መንግሥቱ ያፈነገጠው ህወሓት ዛሬ በትግራይ፣ መቀለ ከተማ በርካታ የክልሉ የልዩ ኃይል አባላትና ታጣቂ ሚሊሻዎች ዓላማው ምን እንደሆን ያልለየ ወታደራዊ ሰልፍ በማካሄድ ትዕይንት አካሂዷል።
በህወሓት ቀጥተኛ ትእዛዝ በሰልፉ ላይ የተሳፉት የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላቱ፣ ቀላልና ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቀው በወታደራዊ ትዕይንቱ ላይ ደፋ ቀና ሲሉ ታይተዋል።
በትግራይ ክልል ዋና ከተማ በመቀለ ጎዳናዎች ላይ ዛሬ ረፋድ በሰልፍ ሲጓዙ የታዩት ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱት የልዩ ኃይሉ አባላትና ሚሊሻዎች፤ በከተማው ወደሚገኘው ስታድየም በመጓዝ ተከማችተው ታይተዋል።
በመቀሌ ከተካሄደው ከዚህ ወታደራዊ የሰልፍ ትዕይንት ባሻገር፣ በሌሎችም የክልሉ ከተሞች ጭምር መደረጉ እየተነገረ ይገኛል።
 ዛሬ የተካሄደው ወታደራዊ ሰልፍ ዓላማው ምን እንደሆነ የትግራይ ክልል መንግሥት የገለጸው ነገር ባይኖርም የተለያዮ የፖለቲካ ተንታኞች አቅሙ እየተሽመደመደ የሚገኘውና ግራ የተጋባው፣ ግፈኞችንና ሌቦችን ያቀፈው ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ በቅርቡ ይደርስብኛል ብሎ ለፈራው ሕጋዊ እርምጃ ራሱን ለማጽናናትና የትግራይ ሕዝብን ለማሳሳት ያደረገው እንደሆነ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
 “ለሰላም ሲባል ለሚከፈል ዋጋ ሁሌም ዝግጁ ነን” በሚል በፌስ ቡክ የሰልፉን ዓላማ ያመላከተው የትግራይ ክልል “የአንድ ሕዝብ የሰላሙ ዋስትና ውስጣዊ አቅሙ እንጂ የማንም የውጭ ኃይል ድጋፍና ጥበቃ ሆኖ አያውቅም” ሲልም ነገሮችን አድበስብሶ ለማለፍ ሞክሯል።
ህወሓት እንዲህ ለጦርነት ሽር ጉድ እያለና ፌደራል መንግሥቱን እየወቀሰ ቢሆንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ሲያደርጉ  “ማን ነው ማንን የሚወጋው? ለምንድነው የፌደራል መንግሥት ትግራይን የሚወጋው? ይህ የእብደት ንግግር ነው። የፌደራሉ መንግሥት የራሱን ሕዝብ የመውጋት ሀሳብና ፍላጎት ፍጹም የለውም” ሲሉም የሚቀርበውን ወቀሳ ማጣጣላቸው አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY