ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ባለፉት ሁለት ዓመታት አስተማማኝ የሆነ ሰላም በራቀው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ቅዳሜ ዕለት ሦስት ሰዎች በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸው ታወቀ።
የክልሉ ሠላም ግንባታና የጸጥታ ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ፣ ታጣቂዎቹ ሦስት የጉባ አካባቢ ነዋሪዎችን እንደወሰዱና እስካሁን የት እንዳሉ አለመታወቁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች እገታው የተፈጸመው ቅዳሜ ዕለት እንደነበር የገለጹት ሓላፊው፤ ታጋቾቹ የጉሙዝ ብሔረሰብ እንደሆነና ሰዎቹ የደረሱበት ባለመታወቁ ቤተሰቦቻቸው ለአካባቢው ባለሥልጣናት ሪፖርት እንዳደረጉ አስታውቀዋል።
የጉባ ወረዳ ነዋሪዎች የሆኑትን ግለሰቦች ታጣቂዎቹ ያገቷቸው “ለመንግሥት መረጃ ትሰጣላችሁ” ከማለታቸው ባሻገር የቤተሰብ አባሎቻቸው ከአካባቢው መስተዳደሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመጥቀስ መታገታቸውን ቤተሰቦቻቸው መመስከረቻውን የፀጥታ ሓላፊው አረጋግጠዋል።
“ታጋቾቹ ስላሉበት ሁኔታ የታወቀ ነገር የለም። ስላሉበት ሁኔታ እርግጠኞች አይደለንም፤ ነገር ግን ተይዘው በተወሰዱበት አቅጣጫ የመከላከያ ሠራዊት ተሰማርቶ ታጣቂዎቹን ለመያዝና ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው” ነው ያሉት እኚህ አመራር፤ እገታው ከተፈጸመ በኋላም መከላከያ እና ልዩ ኃይል ታጣቂዎቹ ተደብቀውባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ላይ አሰሳ በማድረግ በርከት ያሉ አጋቾች እንደተገደሉ ገልጸዋል።
“ታጣቂዎቹ ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ ውስጥ ስለገቡ የቻሉትን ያህል ጥፋት መፈጸም ነው ፍላጎታቸው። ነገር ግን መውጫ የላቸውም፣ ሠራዊቱ ተሰማርቶ እያሰሰ ነው” ያሉት አቶ አብዱላዚዝ፤ ታጋቾቹን በፍጥነት እንደሚያስለቅቁ አረጋግጠዋል።
በጉባ ወረዳ አቡጃር ቀበሌ ከአንድ ሳምንት በፊት ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመው ቢያንስ 13 ሰዎች ተገድለው ሌሎች ሰዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ ቀደም ባለው ጥቃት ውስጥ ተሳትፈው ከነበሩት ታጣቂዎች መካከል 13ቱ ሲገደሉ 30ዎቹ ደግሞ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ገልጸዋል።