አዲስ አበባ በህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት የደስታ ፕሮግራም ዳግም በንጹሁ ሰንደቅ ዓላማ...

አዲስ አበባ በህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት የደስታ ፕሮግራም ዳግም በንጹሁ ሰንደቅ ዓላማ ደመቀች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– “ድምፃችን ለግድባችን” በሚል መርህ  በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ውኃ ሙሌትን በተመለከተ ደስታቸውን እንዲገልጹ የታቀደው ፕሮግራም በአዲስ አበባ በልዮ ሁኔታ  ግቡን መታ።

ሊፍት ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የእዚህ አካል ፕሮግራምም በመንግሥት ደረጃ በደመቀ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።
መመሪያውንና ዓላማውን በጸጋ የተቀበለው የአዲስ አበባ ነዋሪ ከቀኑ ዐሥር ሰዐት ላይ በያለበት ሆኖ በተለያዮ መንገዶች ደስታውን ሲገልጽ ታይቷል። ኢትዮጵያን የሚገልጻት ንጹሁ ሰንደቅ ዓላማም ዛሬ ከሰዐት በኋላ በበርካታ ቦታዎች በስፋት ሲውለበለብ ታይቷል።
የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት እውን መሆኑ ያስደሰተው የአዲስ አበባ ነዋሪ ለኢትዮጵያውያን የቀረበው ይህንን የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ ደስታውን ከማለዳው ጀምሮ አረንጓዴ ቢጫ ቀዮን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ሲገልጽ ከከሰዐት በኋላ ደግሞ ይህ ስሜት አይሎ ታይቷል።
በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች በልዮ ህብረ ዝማሬ የግድቡን ስኬት ሲያሞግሱ አምሽተዋል። የህዳሴው ግድብን ሕብረተሰቡ ከእለት ጉርሱ እየቀነሰ ያዋጣውን ገንዘብ እንደመዘበሩ የሚነገርላቸው አካላትን እየወቀሰ፣ አሁን ላይ ጥሩ ውጤት ያስገኙትን አካላት ሲያሞካሽ የታየው አዲስ አበቤ ደስታውን ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ገልጿል።
በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም መኪናዎች የውሃ ሙሌቱ የፈጠረባቸውን ደስታ በክላክስ ከመግለጻቸው ባሻገር፣ በመኪኖቻቸው ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ለግድቡ እውን መሆን የሚደረገው ጅምር ጥረት ውጤት ፕሮግራምን ድምቀት ሰጥተውት ታይተዋል።

LEAVE A REPLY