ሸገር ዳቦ ፋብሪካ በነጋዴዎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት ምርቱን ለኅብረተሰቡ ማድረስ አልቻልኩም...

ሸገር ዳቦ ፋብሪካ በነጋዴዎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት ምርቱን ለኅብረተሰቡ ማድረስ አልቻልኩም አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ወደ ሥራ ከገባ ገና አንድ ወር የሞላው የሸገር ዳቦ፣ በነጋዴዎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት ምርቱን በተገቢው ሁኔታ ለኅብረተሰቡ ማድረስ እንዳልቻለ ተሰማ።

ዳቦውን ለማከፋፈል በየሰፈሩ በተቀመጡ የአንበሳ አውቶብስ ሱቆች ውስጥ ፣ ዳቦ ቤት ያላቸው ነጋዴዎች በመምጣት እና ከሻጮች ጋር በመመሳጠር ብዛት ያላቸው ዳቦዎችን አትርፈው ለመሸጥ መግዛታቸውን ተከትሎ አብዛኛው ኅብረተሰብ ከረጅም ሰዓት ሰልፍ በኋላ የዳቦው አቅርቦት ስለሚያልቅ ሳይገዛ የሚመለስበት ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ፋብሪካው አስታውቋል።
ፋብሪካው በኮሚሽን ሥራዎች አለመጠናቀቅ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሰዓት ከ30 ሺኅ እስከ 35 ሺሕ ዳቦ እንዲሁም በቀን 7 መቶ 71 ሺኅ ዳቦ በማምረት ለኢንተርፕራይዞች እያከፋፈለ መሆኑን ገልጾ፤ በዚህም ያለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ ምርት እያመረተ ቢሆንም በአንዳንድ ስግብግብ እና አልጠግብ ባይ ነጋዴዎች ትርፍ አጋባሽነት ምክንያት የዳቦ አቅርቦቱን በተሳካ ሁኔታ ወደ ኅብረተሰቡ ለማድረስ እንቅፋት እየገጠመኝ ነው ብሏል።
የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ኃይሉ ቡልቡላ “እውነት ሁላችንም ለማኅበረሰቡ ነው ወይ የምንሠራው ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይገባናል” ያሉት የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ኃይሉ ቡልቡላ፤ በእነርሱ በኩል በአንድ ዳቦ እስከ 20 ሳንቲም እየከሰሩ እንደሚሸጡ ጠቁመው፣ “እኛ ይኽን እያደረግን ሳለ ደግሞ ገበያ ውስጥ እስከ ሦስት ብር እየተሸጠ ነው። ይህ የስግብግበ ነጋዴዎች ከፍተኛ ትርፍን የማጋበስ ፍላጎት ማኅበረሰቡን እየጎዳ ነው። እኛም ከስረን ተጠቃሚውም በተባለለት ልክ ሳይጠቀም እየቀረ ነው” በማለት የመንግሥት እቅድ እውን እንዳይሆን ችግር መፈጠሩን ገልጸዋል።
” ፋብሪካው ማኅበረሰቡን ለመጥቀም በተነሳበት ሰዐት በመካከል የሚገቡ አካላት አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል” ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤
የፋብሪካው ሥራ ዳቦውን አምርቶ ለኢንተርፕራይዞች ማከፋፈል እንደሆነና፣ በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀመር የኅብረተሰቡን ችግርን እንደሚፈታ ትልቅ እምነት አለኝ ሲሉ ተደምጠዋል።
ሆኖም ፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጥናት ማድረግ ይገባል ያሉት ባለሥልጣኑ፤ ይህንን ዳቦ በሙሉ አቅም ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚሠራው ሥራ የፋብሪካው ሓላፊነት ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡም ሆነ መንግሥት፣ እንዲሁም በዚህ አገልግሎት ላይ ሓላፊነት የተሰጣቸው አካላት እንደተጠበቀው እየሠሩ መሆኑን መከታተል እና ቁጥጥር ማድረግ እንደመሚገባም አመላክተዋል።

LEAVE A REPLY