ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን የምርመራ ሥራ አጠናቅቂያለሁ አለ።
ይህን ተከትሎምርመራ መጠናቀቁን ተከትሎ እስካሁን ሲታይ የነበረው የጊዜ ቀጠሮ የምርመራ ሰነድ ተዘግቶ አዲስ ወደተከፈተው ቀዳሚ ምርመራ እንዲዛወርለትም ጠይቋል።
“ቀዳሚ ምርመራ ችሎት” የሚባለው ዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ ተቀብሎ ተጠርጣሪው ላይ የተደረገው ምርመራ ተአማኒ መሆኑን ሲያረጋግጥ የማስረጃ ጥበቃ ለማድረግ የሚከተለው ሥርዓት መሆኑ ይታወቃል።
ሕጉን ተከትሎ ቀደም ሲል ይህን የጊዜ ቀጠሮ ሲመለከት የነበረው ችሎት መዝገቡን ዘግቶ ወደ ቀዳሚ ምርመራ ችሎት እንዲመራው የምርመራ ቡድኑ እና ዐቃቤ ሕግ የአራዳ ምድብ ችሎትን መጠየቁ ዛሬ ተሰምቷል።
በአ/አ ከተማ እና አካባቢዋ እንዲሁም በሻሸመኔ ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም በነበረው ብጥብጥ የደረሰውን ውድመት አስመልክቶ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ዘርፉን የተመለከተ 45 ገጽ ያካተተ ማስረጃ ማቅረቡን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፤ ተጠርጣሪው የሀጫሉን አስከሬን በአስገዳጅ መልኩ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ፣ 10 ቀናት በማስለቀስ የምኒልክ ሐውልት ማፍረስ እና ቤተ መንግሥቱን መቆጣጠር ይቻላል የሚል ትእዛዝ መስጠቱን በማስረጃ አረጋግጫለሁ አለ።
ከተጠርጣሪው የተገኙት ሁለት ሽጉጦች ሕገ ወጥ መሆናቸውን ፖሊስ ዛሬ ለችሎቱ አስረድቷል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች ደንበኛችን ፈጸሙ የተባለውን ወንጀል አመላካች ነገር አልሰማንም፤ ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን አቅርቦ እንዲመረምር እና ይህ የምርመራ መዝገብ ተዘግቶ፣ ጉዳዩ በቀዳሚ ምርመራ ይታይ ቢባል እንኳን ተጠርጣሪው የዋስ መብታቸው ይከበር” ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ በቀለ ገርባም ” የፈጸምኩት ወንጀል የለም፤ እኔ የፖለቲካ መሪ እንጂ የምመራው ሠራዊት የለም፤ በመሆኑም በብሔር እና በሃይማኖት ግጭት የተከፈተብኝ ወንጀል እኔን የሚመለከት አይደለም” ሲሉም ተከራክረዋል።
ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው ላይ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት በመቀስቀስ እና በሌሎች ወንጀሎች ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘቱን ጠቁሞ፤ ይህንን ማድረግ የሚቻለው በጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሳይሆን በመደበኛ ክርክር ነውም ብሏል።
ግለሰቡ የተጠረጠሩበት ወንጀል የሰው ሕይወት የጠፋበት እና ከባድ በመሆኑ የዋስትና መብታቸው ሊጠበቅ አይገባም ሲል ለፍርድ ቤቱ የገለጸ ሲሆን ፤ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ መርምሮ ትእዛዝ ለመስጠት ለሐምሌ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።