ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከአገልግሎት ውጪ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ዳግም ወደ በረራ ሊመለስ መሆኑ ተሰማ።
የአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች ከበረራ ውጪ የሆነው አውሮፕላን ዳግም ወደ በረራ ከመመለሱ በፊት ማሟላት ያለበትን ዝርዝሮችን እንዳቀረቡም ቢቢሲን ጨምሮ በርካታ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር ችግር አለበት የሚባለው ይህ አውሮፕላን ዳግም ወደ በረራ ከመግባቱ በፊት ማሟላት ያለበትን ነጥቦች ይፋ አድርጓል።
737 ማክስ ሁለት አውሮፕላኖች ተከስክሰው የ346 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ ከበረራ ከታገደ ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜን ማስቆጠሩ አይዘነጋም።
የተጠየቀውን ዝርዝር ነገሮች አሟልቶ በጎርጎሳውያኑ አዲስ አመት ዳግም ወደ በረራ ለመመለስ ማቀዱን የገለጸው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን፤ የበረራ መቆጣጠርያ ሶፍትዌር ፣ አብራሪዎቹ ማሟላት ያለባቸውን ነገሮች መከለስ እና የውስጥ መስመሮቹን መቀየር ይጠበቅበታል ተብሏል።
የአሜሪካ አቪየሽን አስተዳደር፣ ሁለቱ አውሮፕላኖችን እንዲከሰከሱ ያደረጉትን ችግሮች በበቂ ሁናቴ ማስተካከሉን የገለጸው ቦይንግ ካምፓኒ፤ አቪየሽኑ ያቀረበው ምክረ ሀሳብ ይፋ ከሆነ እና ቦይንግ ለውጦቹን ካደረገ በኋላ አውሮፕላኖቹ ለበረራ ዝግጁ ይሆናሉ ሲል አስታውቋል።
የቦይንግ የዲዛይን ማሻሻያ ለአየር መንገዶች በተሸጡት አውሮፕላኖች እንዲሁም ገና ባልታዘዙትና ባልተሠሩት ላይ ሊደረግ እንደሚገባ እየተነገረ ነው።
“ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ወደ በረራ ለመመለስ እየሠራን ነው፣ ከአቪየሽን ባለሥልጣኑና ሌሎች ዓለም ዐቀፍ ተቆጣጣሪዎች ጋር በቅርበት እየሠራን ነው። ገና ከፊታችን ብዙ ሥራ ይቀረናል፣ ይህ ፈቃድ በማግኘቱ ሂደት ላይ ወሳኙ ምዕራፍ ነው” ነው ያሉት የቦይንግ ካምፓኒ ቃል አቀባይ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ቦይንግ 737 ማክስ በጎርጎሳውያኑ 2021 ላይ ዳግም ወደ በረራ ይመለሳል ተብሎ ቢጠበቅም፣ አየር መንገዶች ግን አሁንም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በተጣለው ገደብ የተነሳ የተጓዦች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንደ ቀነሰባቸው ታውቋል።