ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ያለ ምርጫ ቦርድ ፍቃድና እውቅና ሥድሥተኛውን የክልል ምርጫ እንዳያካሂድ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወሰነበት የትግራይ ክልል ጉዳዮን አስመልክቶ ምላሽ ሰጠ።
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በሰጡት የደብዳቤ ምላሽ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተጻፈው ውሳኔ በሌለበት እና ክልሉ ምርጫ ይራዘምልኝ ብሎ ባልጠየቀበት ሁኔታ እንደሆነ ጠቁመው፤ ክልሉ የምርጫ ሕግ የማውጣት፣ ምርጫ ኮሚሽን የማቋቋም እና ምርጫ የማካሄድ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን አለው ብለዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና ፌደራል መንግሥት በክልሉ ሕገ መንግሥታዊ መብት ጣልቃ እየገቡ ስለሆነ በዚሁ ጣልቃ ገብነት ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂዎቹ እነርሱ ብቻ ይሆናሉ ሲሉም አፈ ጉባዔው አስጠንቅቀዋል።
“የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚያካሄደው ምርጫ ሓላፊነትን መወጣት እንጂ ከፍላጎት የሚመነጭ አይደለም” በማለት የክልሉን መንግሥት አቋም በደብዳቤያቸው ያሰፈሩት አፈ ጉባዔው፤ ይህ የክልሉ መንግሥት ውሳኔ በክልሉ ህገመንግሥት መሠረት የተመሠረተ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ህገ መንግሥቱ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ እንዲደረግ ስለሚያስገድድ ምርጫ ማካሄድ ለህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ዋስትና መስጠትና ሓላፊነትን መወጣት ያሳያል እንጂ፣ ለህገመንግሥቱ አደጋ ሊሆን አይችልም በማለት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተላከው ደብዳቤ ህወሓት እየተጓዘበት ያለው መንገድ ትክክል እንደሆነ ለማሳየት ሞክሯል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግሥት ትርጓሜ ሰበብ ምርጫ ለማራዘም ያሳለፈውን ውሳኔ “ኢ ህገ መንግሥታዊ” ነው የሚሉት የትግራይ ክልል ም/ቤት አፈ ጉባዔ የክልሉ ምክር ቤት ምርጫ ለማራዘም ምንም ዓይነት ህገመንግሥታዊ ሥልጣን የሌለውን ያህል የትግራይ ክልልም የጣሰው ምንም ነገር የለም ብለዋል።
ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ክልሎች ምርጫ ይራዘምልኝ በማለት ጥያቄ ያላቀረቡ በመሆናቸው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ባልቀረበለት ጥያቄ ውሳኔ መስጠትና ማስፈፀም አይችልም ሲልም የመልስ ደብዳቤው ያስረዳል።
የአገሪቱ ህገ መንግሥት አንቀጽ 9(3) ዋቢ ያደረጉት አፈ ጉባዔው፤ መንግሥት የሚመሰረተው በምርጫ መሆኑን ካስረዱ በኋላ፣ ይህ አንቀጽ በክልሉ ህገ መንግስት ገዢ፣ አስገዳጅና የማይጣስ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
በህገመንግሥቱ አንቀጽ 56 እና 73 አንድ ፓርቲ ሥልጣን መያዝ ያለበት በምርጫ አብላጫ ድምጽ ካገኘ መሆኑን በመጥቀስ ከዚህ ህገ መንግሥት አንቀጽ ውጪ ሥልጣን መያዝ አይቻልም ሲሉም የትግራይ ክልል መንግሥት አቋሙን ይፋ አድርጓል።