የሚሊኒየም አዳራሽ 380 የጽኑ ሕሙማን አልጋዎች በመሙላታቸው ችግር መፈጠሩ ተሰማ

የሚሊኒየም አዳራሽ 380 የጽኑ ሕሙማን አልጋዎች በመሙላታቸው ችግር መፈጠሩ ተሰማ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በትልቅነቱ የሚታወቀው ሚሊኒየም አዳራሽ የኮሮና ቫይረስ ማገገሚያ ማዕከለ ኦክሲጅን አልጋዎች ዕጥረት ማጋጠሙ ታወቀ።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ቫይረሱ ለተገኘባቸው ሰዎች ማከሚያ እንዲሆንየተደራጀው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል መሙላቱን ተከትሎ ነበር የሚሊኒየም አዳራሽ ወደ ለይቶ ማከሚያነት የተዋቀረው።
በአዲስ አበባ የኮቪድ 19  ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱን ተከትሎ ወደ ማገገሚያ ማዕከል የሚገቡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በየጊዜው እያሻቀበ በመምጣቱ የጽኑ ህመምተኞች ቁጥር እንደጨመረ ታውቋል።
 እነዚህን በቫይረሱ በጽኑ የተያዙ ዜጎችን በህይወት ለማቆየት ሲባል የኦክስጂን አልጋዎች ፍላጎት በማየሉ ምክንያት የጽኑ ሕሙማን ክፍል እጥረት ማጋጠሙን መረዳት ችለናል።
የሚሊኒየም የኮቪድ19 ማገገሚያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር እስማኤል ሸምሰዲን በአሁኑ ሰዐት ወደ ማገገሚያ ማዕከሉ የሚገቡ የጽኑ ሕሙማን ታካሚዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የኦክሲጂን አልጋዎችን እንዲጠቀሙ ማስፈለጉን ተከትሎ  በጽኑ ህሙማንን የሚያስተናግዱ የኦከሲጂን አልጋዎች እጥረት በከፍተኛ ተከስቷል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ ወቅት ማዕከሉ በአጠቃላይ 600 የሚሆኑ ታካሚዎች እያስተናገደ ቢሆንም ከ 300 በላይ የሚሆኑት የኦክስጅን ታካሚዎች መሆናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በአጠቃላይ በማእከሉ የሚገኘው የኦክስጂን አልጋ 380 ብቻ ቢሆንም ይህ ቁጥሩ በየሰዐቱ እንደሚቀያየርና   አሁንም ቢሆን የኦክሲጅን አልጋዎች የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ቁጥር በመጨመሩ ሁኔታውን እጅግ ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል።
 ማዕከሉ ወደ ሥራ ሲገባ በቀን ያስፈልግ የነበረው 10 ሲሊንደር ኦክስጂን በአሁኑ ሰዐት በቀን ወደ 100 ሲሊንደር ኦክስጂን ከፍ ማለቱ ለዚህ ማሳያ መሆኑን ያስረዱት የጤና ባለሙያው፤ በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ይህ የጽኑ ሕሙማን ቁጥር ለማሻቀቡ በዋናነት ህብረተሰቡ ያለው ቸልተኝነት መሆኑን ገልጸዋል።
  በተለይም ወጣቶች ተያያዥ ህመም ያሉባቸውን ቤተሰቦቻቸውን ከልብ የሚወዱና በህይወት እንዲቆዩላቸው የሚፈልጉ ከሆነ ፣ በአጠቃላይ ለቤተሰቡ እና ለራሱ ህይወት የሚጨነቅ የሰው ፍጡር ሁሉ ይህንን ቫይረስ ለመከላከል ጥረት ሊያደርግ እንደማገባም የማዕከሉ ዳይሬክተር መልእክት አስተላልፈዋል።

LEAVE A REPLY