ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ባህር ዳር ከተማና በአንዳንድ የአማራ ክልል ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች፤ የወባ በሽታ መከላከያ መድኃኒትን ለኮሮና ቫይረስ መድኃኒትነት ያገለግላል በሚል በከፍተኛ ሁኔታ እየገዙ እን ያልተረጋገጠ መረጃ እየገዙ ነው ተባለ።
ከወባ መድኃኒቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን “ክሎሮኪን” የተሰኘውን መድኃኒት ሕብረተሰቡ በከፍተኛ ወጪ እየገዛ ነው የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ሕብረተሰቡ ይህንን መደኃኒት እንደ መጠባበቂያ በማሰብ በስፋት እየገዛ መሆኑን ተከትሎ፣ ቀደም ሲል በመድኃኒት መደብሮች 150 ብር ሲሸጥ የነበረውና በውስጡ አንድ መቶ ኪኒኖችን የያዘ አንድ ካርቶን የወባ መድኃኒት፣ አሁን እስከ 900 ብር እየተሸጠ ነው ብለዋል።
አንዳንድ መድኃኒት ቤቶች የሕብረተሰቡን ፍላጎት መጨመር በመመርኮዝ ወደ ፊት የመድኃኒቱ ዋጋ ሊጨምር ይችላል በሚል አከማችተው እስከ ማስቀመጥ መድረሳቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የባህርዳር እና አካባቢው ነዋሪዎች፤ ወቅቱ የወባ በሽታ የሚቀሰቀስበት ጊዜ ባለመሆኑ “ክሮሊንክ”ን ለኮሮና መድኃኒትነት ይሆናል በሚል ሕዝቡ በገፍ መግዛቱ ከፍተኛ የሆነ ዕጥረት እንዲከሰት ማድረጉንም አስታውቀዋል።
በአካባቢው ችግሩ እንዳለ የሚያሳዮ የተለያዮ ጥቆማዎች መኖራቸውን ያመላከቱት በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽ/ፈት ቤት ሓላፊ አቶ ሙልጌታ ቆየ ፤ ነዋሪዎች መድኃኒቱን ገዝተዋል ቢባልም አስከ አሁን ግን የወባ መድኃኒት ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ያገለግላል ተብሎ ሲሸጥ አልተገኘም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በግላቸው መድኃኒቱ ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ያገለግላል ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደሚያውቅ ያልሸሸጉት አቶ ሙልጌታ፤ ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ወደ ፊት በሚደረግ ማጣራት በባለሙያዎችና በግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድና ሕብረተሰቡ አሜሪካ የወባ መድኃኒት ለኮሮና ቫይረስ በሽታ መድኃኒትነት እንደሚያገለግል መግለጿን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጩ መረጃዎች አማካይነት ክፍተቱ መፈጠሩን ገልጸዋል።
በባህር ዳርና አካባቢዋ እንቅስቃሴ በመቆሙ ጉዳዩን በትኩረት ለመከታተል አስቸጋሪ እንዳደረገው ያስረዱት ሓላፊው፤ በኢትዮጵያ ማንኛዉም አይነት መድኃኒት በብሔራዊ አማካሪ ኮሚቴ ታይቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ካልተፈቀደ በምንም መልኩ መጠቀም የተከለከለ መሆኑን ሕብረተሰቡ ሊረዳው ይገባል ብለዋል።