ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ህወሓት መራሹ የትግራይ ክልል ምክር ቤት የምርጫ ሥርዓት ለውጥና በምክር ቤቱ ውስጥ ባለው የመቀመጫ ብዛት ላይም የቁጥር ጭማሪ ማድረጉን አስታወቀ።
ዛሬ ስብሰባ ያረገው ምክር ቤቱ በስብሰባው የክልሉን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48ን በማሻሻል የትግራይ ክልል ምክር ቤት የመቀመጫ ቁጥር እንዲጨምር በመወሰን ሢሠራበት እስካሁን የነበረውን የምርጫ ሥርዓት ማሻሻሉ ተሰምቷል።
በውሳኔው መሠረት በክልሉ ከዚህ በፊት የነበረውን የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ሥርዓት በመቀየር በ”ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት” እንዲተካ በማድረግ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
በተጨማሪም በምክር ቤቱ ውስጥ ካሉ መቀመጫዎች ውስጥ 80 በመቶዎቹ የአብላጫ ድምጽ ባገኘው የፖለቲካ ድርጅት የሚያዙ ሲሆን፣ 20 በመቶው ደግሞ በተመጣጣኝ ውክልና ለተወዳዳሪ ድርጅቶች እንደሚከፋፈል ምክር ቤቱ አስታውቋል።
እስካሁን ድረስ በክልሉ ምክር ቤት የነበረው የመቀመጫ ብዛት 152 ሲሆን፤ በማሻሻያው መሰረት አሁን 38 መቀመጫዎች ተጨምረው ወደ 190 ከፍ እንዲል ተወስኗል።
ዛሬ በጸደቀው የመቀመጫ ድልድል መሠረት የተጨመሩት 38 መቀመጫዎች ወይም ከአጠቃላዩ የምክር ቤት መቀመጫ 20 በመቶው በምርጫ የተወዳደሩ ድርጅቶች ከተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች የሚያገኙት ድምጽ ተሰብስቦ ባገኙት የድምጽ ብዛት አንጻር የሚከፋፈሉት ይሆናል ተብሏል።
ምክር ቤቱ እንዳለው እነዚህ ድርጅቶች የተመደቡትን መቀመጫዎች ለመከፋፈል የሚችሉት ቀድመው የተወካዮቻቸውን ስም ለምርጫ ኮሚሽኑ ማገስባት ሲችሉ ነው ያለው የትግራይ ክልል ም/ቤት፤ እነዚህ መቀመጫዎች ለተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ የተተዉ ስለሆኑ፣ የግል ተወዳዳሪዎች ከ38ቱ መቀመጫዎች ምንም ድርሻ አይኖራቸውም ተብሏል።