በህወሓት ጥሪ ኮሮናን በመከላከል ዘመቻ የነበሩት ተባባሪ ፕ/ር ፍሰሃየ አለምሰገድ በቫይረሱ ሕይወታቸውን...

በህወሓት ጥሪ ኮሮናን በመከላከል ዘመቻ የነበሩት ተባባሪ ፕ/ር ፍሰሃየ አለምሰገድ በቫይረሱ ሕይወታቸውን አጡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት በኢፒዲምዮሎጂ ትምህርት ክፍል ባልደረባ የነበሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ፍሰሃየ አለምሰገድ ተስፋሚካኤል ኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ለመከላከል ሙያዊ እገዛ እያደረጉ ባለበት ወቅት በቫይረሱ ተይዘው ሕይወታቸው ማለፉ ተነገረ።
ዶክተር ፍሰሃየ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ የሕክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ቢቆይም ዛሬ ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።
ዶ/ር ፍሰሃየ አለምሰገድ በ1970 ዓ.ም በትግራይ ክልል ዓድዋ ወረዳ ልዩ ስሙ ይሓ በተባለ ቦታ ተወልደው ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የሕክምና ትምህርታቸውን በስኬት በመጨረስ በጠቅላላ ሐኪምና በኅብረተሰብ ጤና የኢፒዶሞሎጂ የማስተርስ ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።
ዶ/ር ፍሰሃየ አለምሰገድ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመምህርነት፣ በተማራማሪነትና በሙያ እማካሪነት ከ1994 ዓ/ም እስከ 2011 ዓ/ም ያገለገሉ ሲሆን፣ ከመስከረም 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አክሱም ዩኒቨርሲቲ በመዛወር በዩኒቨርሲቲው የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ሢሠሩ ነበር።
 በእናቶችና ሕጻናት ሕክምና፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች፣ በስነ-ምግብ፣ በወባ፣ በኤች አይቪ ኤድስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ጨምሮ በሌሎች የኅብረተሰብ ጤና ዘርፎች ከ50 በላይ ችግር ፈቺ ጥናቶችን በታዋቂ ጆርናሎች በማሳተም፣ አዳዲስ እውቀቶች በማፍለቅ ለዓለም አሻራቸውን ያሳረፉ ምሁር ነበሩ- ዶክተር ፍሰሃየ አለምሰገድ።
ግለሰቡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ፈጣን ግብረ መልስ ቡድን መሪ በመሆን ህዝባቸውን ከቫይረሱ ለመታደግ  ሢሠሩ ቆይተው (ህወሓት) የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ ባደረገላቸው ጥሪ በኮሮና ቫይረስ መረጃ ትንተና እና ትንበያ ክፍል በመሥራት ላይ እያሉ ለኮሮና ቫይረስ በመያዛቸው ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።

LEAVE A REPLY