ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እየቀነሰ መምጣቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት እና የመሠረተ ልማት በተፈለገው አቅም አለመሟላቱ ለችግሩ መንስዔ ሆነዋል ያለው መረጃ፤
የተጠቀሱት ምክንያቶች በኢንቨስትመንቱ ላይ ጫና እንደፈጠሩም አስታውቋል።
ባለፉት 5 ዓመታት በአጠቃላይ 16.25 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት መመዝገቡን የጠቆመው ኮሚሽኑ፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሥራ አፈጻጸም ከሀገራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር አሁንም የተፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱንም ይፋ አድርጓል።
ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን ምክንያት ናቸው ከተባሉት ጉዳዮች ውስጥ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሬ ማጠር እና በቂ የሆነ ግብዓት አለማቅረብ፣ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ የሚሆን የሰው ሀብት አለመኖር በቀዳሚነት ተቀምጠዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ሥራ አለመግባታቸው በሁለተኛነት የሚጠቀስ ምክንያት መሆኑን ኮሚሽኑ በመግለጫው ላይ አስቀምጧል።
የፀጥታ አለመኖር፣ ፕሮጀክቶችን ወደ ምርት በማሻገርና ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ሥራ ላይ ችግር እንዳመጣ ያስረዳው ኮሚሽኑ፤ ለኢንቨስትመንት ሥራ የሚውል የመሬት አቅርቦት በቂ አለመሆን እና ለባለሀብቶች ጥያቄ የፈጠነ መልስ አለመሰጠትም ትልቅ እንቅፋት ሆኖብኛል ብሏል።
በየጊዜው የሚደረጉ የሥራ ማቆም አድማ መምታት በምርት አገልግሎት እና በኤክስፖርት ሥራ ላይ ችግር አምጥቷል ያሉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሥልጣናት፣ ከክልል የዘርፉ ሓላፊዎች እና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላተ ጋር ችግሮቹን ለመቅረፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ይገኛሉ።
ከመሬት አቅርቦት አንጻር ችግር መኖሩ፣ ከአቅርቦት ችግር ባሻገር የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ መሬቶች ቶሎ ወደ ሥራ አለመግባታቸውም ተጨማሪ የዘርፉ ራስ ምታት መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ተናግረዋል።