በድሬደዋ ከተማ 21 የሕክምና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

በድሬደዋ ከተማ 21 የሕክምና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 21 የሕክምና ባለሙያዎችና በጤና ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተነገረ።

የከተማዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ወ/ሮ ስንታየሁ ደበሳ ፤ በሕክምና ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸው እተደረገ ያለውን ወረርሽኙን የመከላከል ሥራ ላይ እንቅፋት እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የጤና ባለሙያዎቹና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቹ ለኮሮና ቫይረስ የተጋለጡት በሥራ ቦታቸው ላይ እያሉ ሲሆን፤ ለጤና ባለሙያዎቹ በሽታውን ለመከላከል አስፈጊ የሆኑ አቅርቦቶችን በተመለከተም አስተዳደሩ በበቂ ሁኔታ እያቀረበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እስካሁን ድረስ ያጋጠመ እጥረትና ችግር የለም ተብሏል።
ይሁን እንጂ በየሕክምና ተቋማቱ የሚኖሩ ንክኪዎች ባለሙያዎቹን ለቫይረሱ አጋልጧል የሚሉት የከተማ አስተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነት ፤ ከባለሙያዎቹ ጋር በተደረገ ውይይት እንደተናገሩት ከሆነ ለቫይረሱ የተጋለጡት በየትኛው ጊዜ እንደሆነ ለማለየት ተቸግረዋል።
በሕክምና ተቋማቱ ያሉ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት ግን  ድጋፍ ሰጪዎቹና የሕክምና ባለሙያዎቹ ሥራ ላይ እያሉ ተጋላጭ መሆናቸውን ነው መረዳት ይቻላል ያሉት ወ/ሮ ስንታየሁ፤ ባለሙያዎቹ እየወሰዱ ያሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መፈተሽ እንደሚያስፈልግም ጎን ለጎን አንስተዋል።
“የጤና ባለሙያዎቻችን በቫይረሱ እየተያዙ መምጣት ወረርሽኙን ለመከላከል የምናደርገውን ጥረት ያዳክማል” ያሉት ሓላፊዋ፤ በቫይረሱ ከተያዙት የሕክምና ባለሙያዎች መካከል በድንገተኛ እና በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚሠሩ ነርሶችና ዶክተሮች እንደሚገኙበትም አረጋግጠዋል።
የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ከገባበት ወርሀ መጋቢት አንስቶ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ስምንት ሺኅ የሚደርሱ ሰዎች ናሙናዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ መደረጉን ተከትሎ፤ ከ500 በላይ ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸውንና 20 ያህል ሰዎች ደግሞ በኮሮና ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በአንጻሩ በከተማ አስተዳደሩ ከ400 በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ማገገማቸውን ከሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው መግለጫ መረዳት ተችሏል።

LEAVE A REPLY