ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በቢሾፍቱ ከተማ ከሀጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ ኹከት እንዲፈጠር አድርገዋል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉትና ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት የአዴፓ አባሉ አቶ ልደቱ አያሌው ተጨማሪ የ7 ቀናት ቀጠሮ ተሰጣቸው።
የኢዴፓ ፓርቲ ፕሬዝደንት አቶ አዳነ ታደሰ ፤ “ፍርድ ቤቱ ፖሊሶች የደረሰቡትን መረጃ ጠይቆ ፖሊሶች ከ14 ቀናት ጊዜ በኋላ ከቃል አቤቱታ ውጭ ማቅረብ አልቻልንም ተጨማሪ 14 ቀናት ይሰጠን ብለው ጠይቀዋል። ይህን የተመለከተው ፍርድ ቤት ለመጨረሻ ጊዜ የ7 ቀናት የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ሰጥቷል።” ሲሉም አረጋግጠዋል።
“አቶ ልደቱ የልብ ህመምተኛ እንደሆኑና የሕክምና ሰርቲፌኬት እንዳላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተው እስካሁን ግን ፍርድ ቤቱ ከዚህ በፊት ሕክምናቸውን እንዲከታተሉ የወሰነው ውሳኔ ተፈፃሚ አልሆነም። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ በጠየቁት መሠረት ፍርደ ቤቱ በአቅራቢያው ከሚገኘው ሆስፒታል ለሚቀጥለው ቀጠሮ የሕክምና ማስረጃ ይዘው እንዲቀርቡ የሚል ትዕዛዝ ሰጥቷል።” ያሉት የኢዴፓ ፕሬዝዳንት፤ አቶ ልደቱ አያሌው ነሐሴ 11/2012 ዓ.ም ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡም ተናግረዋል።
አወዛጋቢው ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ነዋሪ ሲሆኑ፣ የፌደራል ፖሊስ ስልካቸው ላይ በመደወል እንደሚፈለጉ በገለጸላቸው መሠረት ወደ ፌደራል ፖሊስ ቢሮ በመሄድ እዚያ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ፌደራል ፖሊስም ለሚፈልጋቸው የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ካስረከባቸው ሳምንታት ተቆጥረዋል።
በተያያዘ ዜና ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ቢጠይቅባቸውም ችሎቱ ተጨማሪ የ9 ቀናት ጊዜ መፍቀዱ ታውቋል።
የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ አሁን ላይ የኢኃን ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ኢንጂነር ይልቃል ከታሰሩ አንድ ወር ከአምስት ቀን እንደሆናቸው ጠበቃቸው አዲሱ ጌታነህ ገልጸዋል።