ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተነሳው ግርግርና አለመረጋጋት ቢያንስ የአስር ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ወላይታ ዞንን በክልልነት ለማደራጀት ከተቋቋመው ሴክሬታሪያት ስብሰባ ተሳታፊ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የህግ ባለሙያዎችና የአገር ሽማግሌዎች በቁጥጥር ሥር በመዋላቸው ነበር ኹከቱ የተቀሰቀሰው።
እሁድ እለት አለመረጋጋቱ ከፍተኛ እንደነበር በተነገረበትና ከሶዶ ከተማ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቦዲቲ ከተማ ፣ የሟቾች ቁጥር ከሠባት በላይ እንደሆነ፤ በሶዶም ሰዎች መገደላቸውን የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ማቴዎስ ባልቻ ገልጸዋል።
ከሆስፒታል የተሰባሰቡ መረጃዎችንና ከአካባቢው ነዋሪዎች ደረሰኝ ያለውን መረጃ ዋቢ ያደረገው ንቅናቄው፤ በሶዶ ሦስት ሰዎች እንደሞቱና በቦዲቲም ሌሎቹ እንደተገደሉ ገልጿል።
“የሚያሳዝነው የተገደሉት ልጆች ጠንከር ያለ አርጩሜ ይበቃቸው ነበር። አስለቃሽ ጋዝም መርጨት ይቻል ነበር። አንዳንዶቹ እየሮጡ አሳዶ መተኮስ በጣም የሚያሳዝን ነው” ሲሉ አቶ ማቴዎስ ቢናገሩም፤ የክልሉ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር የግለሰቦቹ ሕይወት የጠፋው መሳሪያ ለመንጠቅ ባደረጉት ትንቅንቅ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ውስጥ ከትናንት በስቲያ በጥይት ተመትቶ የመጣ አንድ ግለሰብ ሕይወቱ ማለፉን ያጣራው ቢቢሲ፤ ግለሰቡ የ30 ዓመት እድሜ እንደሆነ የጠቆሙ የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያ ሦስት ግለሰቦችም በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙ ማረጋገጣቸውን ዘግቧል።
የ22 ዓመት እድሜ ያለው አንደኛው ግለሰብ በጥይት አንገቱ ላይ ተመትቶ በፅኑ ህክምና ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ በከፋ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም እኚሁ የጤና ባለሙያ ጠቁመው፤ ሌላኛው የ25 ዓመት ጎልማሳ እንደሆነና እግሩ ላይ በጥይት ተመትቶ ደም ስሩም በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱን፣ በተጨማሪም ሌላኛው ህመምተኛ በጥይት ሳይሆን በዱላ በከፍተኛ ሁኔታ መደብደቡን አረጋግጠዋል።
ከፅኑ ማቆያ ህሙማን ክፍል በተጨማሪም ሦስት ግለሰቦችም በጥይት ተመትተው የአጥንት ህክምና ክፍል ውስጥ ተኝተው እየታከሙ ቢሆንም፤ ሆስፒታል ውስጥ መጥቶ ህይወቱ ያለፈ እንደሌለና ነገር ግን በቦዲቲ አምስት ሰዎች መሞታቸውን መረጃ ማግኘታቸውን እንዲሁም በሶዶ ከተማም ውስጥ ሌሎች ሰዎች ስለመሞታቸው መረጋገጡን የንቅናቄው መሪ አስታውቀዋል።