ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– እስካሁን በዓለም ዙሪያ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ20 ሚሊየን እንዳለፈ ታወቀ።
በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ዝርዝር መረጃዎችን የሚያቀርበው የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በድረ ገጹ ያወጣው መረጃ እንዳመለከተው ፤ እስካሁን ድረስ በዓለም ዙሪያ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 20 ሚሊየን 90 ሺኅ 541 መድረሱን ያሳያል።
በመረጃው መሠረት በዓለም ላይ 12 ነጥብ 2 ሰዎች ከቫይረሱ ሲያገግሙ፤ 735 ሺኅ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።
ከተጠቀሰው ዝርዝር ውስጥ በአሜሪካ ብቻ 5 ሚሊየን 94 ሺኅ 314 ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው፣ ከ163 ሺኅ በላይ ሰዎች ህይወታቸው በማለፉ ከዓለም ሀገራት ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።
3 ሚሊየን 57 ሺኅ 470 ዜጎቿ በኮሮና ቫይረስ የተያዙባት ብራዚል ሁለተኛ ስፍራን ስትይዝ፤ ከ2 ሚሊየን 268 ሺኅ በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ የተያዙባት ህንድ ሦስተኛ ስፍራ ላይ ተመዝግባለች።
890 ሺህ 799 ዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሩሲያ ደግሞ አራተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፤ 563 ሺህ 595 ዜጎቿ በቫይረሱ የተያዙባት አፍሪዊቷ ሀገር ደቡብ አፍሪካ በዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።