ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሲዳማ ክልል ያለው ግዙፉ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ከ100 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩ ተሰማ።
የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ማቴ መንገሻ ፤ በኢንደስትሪ ፓርኩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን የተረጋገጠው፤ አንድ ሠራተኛ ከ12 ቀን በፊት ታሞ በፓርኩ በሚገኝ ክሊኒክ ለሕክምና በመሄዱና ምልክቶቹ የኮሮናቫይረስ መሆናቸው በመረጋገጡ ጥቆማ ደርሷቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ግለሰብ እንዲሁም ከባሕር ማዶ የመጡ የድርጅቱ ሠራተኛ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ሲመረመሩ ከ100 በላይ ሰዎች ተይዘው መገኘታቸውን የጠቆሙት ሓላፊው፤ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ንክኪ አላቸው ተብሎ ከሚታመኑ ሰዎች በአጠቃላይ ናሙና እየተወሰደ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ከፍተኛ ንክኪ አለው ተብሎ የተገመተው አንድ ሼድ ውስጥ ስምንት መቶ ያህል ሠራተኞች በመኖራቸው፤ ሁሉንም ሠራተኞች ለመመርመር ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በአንጻሩ ከሁለተኛው ሼድ ግን ሙሉ በሙሉ አለመወሰዱን የገለጹት ሓላፊው፤ በቫይረሱ ከተያዙት ሠራተኞች መካከል የውጭ አገር ዜጎች፣ የሰው ኃይል አስተዳደር ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችና፣ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ኦፕሬተሮች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በኢንደስትሪ ፓርኩ ያለውን ስርጭት ተቆጣጥረናል ማለት ያስቸግራል ያሉት ዶ/ር ማቴ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውንና ንክኪ ያላቸውን ለመለየት ሥራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የቫይረሱን ስርጭት ባለበት ለማቆም ከኢንደስትሪ ፓርኩ ጋር በመነጋገር ቫይረሱ በስፋት የታየበት ሼድ ለተወሰነ ገዜ ሥራ እንዲያቆምና ሠራተኞች ራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ ለማድረግ ቢታሰብም ውጤታማ መሆን አለመቻሉንም የጤና ቢሮ ከፍተኛ አመራሩ አስረድተዋል።