ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የብልፅግና ፓርቲ መሥራች የሆኑት የዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ የሆነውና 5 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ራዕይ ያነገበው የ2012 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል ተባለ።
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ተሳታፊ በመሆን ባደረጉት ንግግር፤ “ለዓመቱ የክረምት ወቅት የተያዘው 5 ቢሊየን ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር፣ በውቢቷ ሀዋሳ ከተማ ተጀምሮ በውቢቷ ባህርዳር ከተማ ቤዛዊት ተራራ ላይ ተሳክቷል” ብለዋል።
4 ቢሊየን ችግኞችን ባለፈው ዓመት ክረምቱን በሙሉ በተከናወነ መርሃ ግብር መተከሉን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮ 5 ቢሊየን ችግኝ ግን ክረምቱ አንዱ ወር ቀርቶት ማሳካት መቻሉን አብራርተዋል።
እቅዱ ቀድሞ በመሳካቱ ተጨማሪ 200 ሚሊየን ችግኝ ተዘጋጅቷል ያሉት ዶክተር ዐቢይ፤ የዓመቱን የችግኝ መትከል እቅድ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በውጤትም እናሳካዋለን ሲሉ ተደምጠዋል።
ለቀጣዩ ዓመት 2013 ዓ.ምጰበተመሳሳይ 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል መወጠኑን ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዘንድሮውም ሆነ ካለፈው ዓመት ለየት ባለ መልኩ ለጎረቤት ሀገራት 1 ቢሊየን ችግኝ እንደሚዘጋጅ ይፋ አድርገዋል።
በ2014 ዓ.ም ወይም በአራተኛው ዙር ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተክሉት ችግኝ 20 ቢሊየን እንደሚደርስም የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ 20 ቢሊየን ችግኝ የመትከል እቅድ ስኬታማ በሚሆንበት ወቅትም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሪባን ይቆረጣል ብለዋል።
ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የማቀድ፣ የማለም እና የማሳካት እቅዳችን እያደገ ሲሄድ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ ወጥታ የምናይበት እንደሚሆን እምነቴ ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቃ ሳንነካ የምናበልፅገው ሀገር እንደሌለ አውቆ፣ ችግር ሳንጋፈጥ የምንቀይረው ሀገር እንደሌለ አውቆ፣ በሽታው መፍረሱም በጭንቅላታችን መሆኑን አውቆ፣ በጭንቅላት ውስጥ ያለውን ካንሰር በማፅዳት ይህችን ታላቅ ሀገር አንድነቷ እና ብልፅግናዋን ማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ያበርክት” ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።