አንዷ ወፍ እየበረረች ሂዳ በሳርና በለቃቀመችው ስንጥር የጨረቃ ቤት ሰርታ አረፍ ትላለች …እና ወፍ ጎጆ መስራቱ ምን ይገርማል…? ምንም አይገርምም! የዚችን ወፍ ለየት የሚያደርገው ጎጆዋን የቀለሰችው እንደዘመድ አዝማዶቿ ዛፍ ላይ ሳይሆን የቆመ መኪና ላይ መሆኑ ነው … መቸም ተበላሽቶ ለአመታት የቆመ መኪና መስሏችሁ አሁንም ‹ምናለብት › እያላችሁ ይሆናል …. ፅድት ያለ ከአምስት ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ አዲስ ሞዴል ማርቸዲስ /Mercedes-AMG G63 SUV/ መኪና ላይ ነው የኔ ጌታ ! ይሄም አይደለም ዋናው ጉዳይ !ወፏ ጎጆ የቀለሰችው የዱባዩ ልዑል የሸህ ሀምዳን መኪና ላይ ነው !
ልዑሉ መኪናውን ወዳቆመበት ጎራ ሲል ይች ወፍ ኮፈኑ ላይ በደለደለችው ጎጆ ላይ ዘና ብላ ተኝታ ያያታል … ምናለ? መቸም ሁላችሁም በአንድ አፍ ‹‹እሽ አላት ›› ብላችሁ ይሆናል… ወይም አንች ሰፋሪ ዳይ ወደክልልሽ ወላ ወደዛፍሽ …. ! ሁለቱንም አላለም ወደጠባቂዎቹ ዙሮ !….‹‹አትረብሸዋት!›› ነው ያለው ! በቃ አዘዘ ባለቤቱ …<<አንድ ሰው ይችን ወፍ እሽ ይላትና ውርድ ከራሴ ! ›› እና ይሄው ይች ወፍ እንደውም አካባቢው ዙሪያውን እንደምታዩት ታጥሮላት ደብሯት አልያም በቃኝ ብላ ካልሄደች በስተቀር መኪናው ላይ ትኖር ተብሏል ! ‹‹የሸህ ሀምዳን ወፍ ›› ብሏታል ታዛቢው!
ዓለም ዓይነውሃው አላማረንም እያለ ወንድሙን ከዓመታት ርስቱ ሲያፈናቅልና ሲገድል …በህገወጥ ግንባታ ስም ከነቤቱ እየመነገለ የትም ሲያፈሰው ….እንዲህ ያለላት ወፍ ጎጆዋን የሚሊየን ብሮች መኪና ላይ ቀልሳ በክብር ትኖር ዘንድ የላይኛው አዞላታል ! <<እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? >> ይላል መፅሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ ወንጌል 6 ፡26