የተከበራችሁ የኦሮሞ እናትና አባቶቼ በያላችሁበት የከበረ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ፡፡ እንደምን አላችሁ? ደህና ናችሁ?
እንዲህ ህልም ይሁን ፊልም ቅጡ በጠፋበት በዛሬውየኢትዮጵያ የእብደት ዘመን ላይ ሆኜ የእናንተ ድርሻ ጉልህ የነበረበትን ደጉን የልጅነት ዘመኔን ሳስብ ደስታዬ ወሰን ያጣል፡፡ አንዳንዴም እዛው ሀሳብ ላይ ቆሞ መቅረት ያምረኛል፡፡ ይብላኝ ያንን የመሰለ ፍቅርና መከባበር ማየት ላልታደሉት የዘመኑ/የብልፅግና ልጆች፤ ደግሞም ወዮላቸው ለእነኛ አይተው አላየንም ሰምትው አልሰማንም ብለው ለካዱ የበሉበትን ወጭት ሰባሪዎች፡፡
እናንተስ ምን ይሰማችሁ ይሆን? እውነት እውነት እላችኋለው ትክክለኛ ስሜታችሁን ለማወቅ ከልቤ እጓጓለሁ፡፡ ይሄ ሁልጊዜ ችግር ከተፈጠረ በኋላ ታስቦበት ለፖለቲካ፣ ለሚዲያ፣ ለካሜራ፣ ለውሎ አበል እና ለበሬ ፍጆታ በስማችሁ የሚዥጎደጎዱትን ባዶ የይቅርታና የተስፋ ቃላት ሳይሆን እውነተኛውን ስሜታችሁን ማወቅ ነው የምፈልገው፡፡
እስቲ ልጠይቃችሁ፣
ድሮ በደጉ ዘመን ልጆቻችሁ ከጎረቤት ልጆች ጋር ሲጣሉ “ከመልካም ጎረቤቶቼ ልታቀያይሙኝ” ብላችሁ የምትገስጿቸው ትዝ ይላችኋል? አንቺ ትብሽ አንተ ትብስ ተባብላችሁ ክፉና ደግ አብራችሁ ያሳለፋችኋቸው ወላጆቻችንም ቢሆኑ እኮ የእናንተን ልጆች ከነካን የቁጣ መአት ነበር የሚያወርዱብን፡፡ ኧረ ዱላም ያቀምሱን ነበር፡፡
ያኔ የአንዱ ልጅ ሲያጠፋ ሌላው አይቶ ዝም አይልም ነበር፡፡ የዚያ ዘመን ወላጅ “ባልወልደውስ ልጄ አይደል እንዴ?” “የእገሊት ልጅ ማለት ያው የእኔ ልጅ ማለት ናት” እያለ የሰፈሩን ልጅ ሁሉ በእኩል ዓይን እያያ ነበር የሚያሳድገው፡፡ ባስ ሲልም ኩርኩም እና አርጩሜም አይቀርልንም ነበር፡፡ “ነበር እንዲሁ ቅርብ ኖርዋል ለካ?” አሉ እቴጌ ጣይቱ፡፡
እናንተ መልካም የኦሮሞ እናቶች እና አባቶች߹ ግን እንደው ለመሆኑ ዛሬ አገራችን ላይ በተለይ በአማራው እና በክርስቲያኑ ላይ ለተከፈተው ግልጽ ጦርነት አድራጊውም ፈጣሪውምየእናንተ የአብራካችሁ ክፋዮች መሆናቸው “እንዴት?“ የሚል ጥያቄ አላጫረባችሁም? ምን ተሰምቷችሁ ይሆን? በበኩሌ ከህያዋንም፣ ከሙታንም፤ ከእንስሳውም፣ ከግዑዙም፤ከምግቡም፣ ከመጠጡም፤ ከነጩም፣ ከጥቁሩም፤ከመንግሥትም፣ ከህዝብም፤ ከእራሳቸውም፣ ከምናቸውም ጋር ሲለተሙ የሚውሉ የጥፋት ሠራዊቶችን አፍርታችሁ ለአገር (ምን ለአገር ብቻ ለዓለምም እየተረፉ ነው) ገፀ-በረከት አቀረባችሁ ብዬ ለማመን በጣም ከበደኝ፡፡ አፈርኩ፡፡ ከእናንተ አብራክ ወጡ ለማትም ተናነቀኝ፡፡ ይህን ማሰብ የበለጠ ያማል፡፡ ስቃዬን ያበዛዋል፡፡ ግን ደግሞ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ እራሴን ለማፅናናት እናንተ ይሄንን ጉድ አልሰማችሁም፤ አላያችሁም፤ ብዬ እራሴን ለማሳመን ወደድኩ፡፡ አልሰማችሁምአይደል? አላያችሁም አይደል?
• እነኛ በዓለምም በሀዘንም ከጎናችሁ ሆነው የኖሩት አብሮ አደግ ወንድም እና እህቶቻችሁ የእኛ ወላጆች በእናንተው ፍሬዎች በገጀራ ተከታትፈው ላይመለሱ መሄዳቸውን፤ ከዚያም አልፎ አስከሬናቸው “የኦሮሞን አፈር“ እንዳይቀምስሲከለከል አላያችሁም፤ አልሰማችሁም፡፡
እንዴ! እኛ እኮ ጨነቀን! እርግጥ ነው ይህን ሁሉ ጉድ ባትሰሙና ባታዩ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን ተወደደም ተጠላም ይህን ሁሉ ሳጥናኤልን ያስቀና ጭካኔ የፈፀሙት ልጆቻችሁ ናቸው፡፡ ጥያቄው እነኚህ ወንበዴ ልጆች ያንን ሁሉ ጥፋት ፈጽመው መተው ቤታችሁ አስገብታችኋቸዋል? ምግብ ሰጥታችኋቸዋል? አሳድራችኋቸዋል? አልተፀየፋችኋቸውም? የሰው ደም ጠምቷቸው ሲክለፈለፉ ስታዩ ምን ተሰማችሁ? እናቶች እውነቱን ንገሩኝ “ምነው ባልወለድናቸው፤ ማህፀናችን ውስጥ ውኃ ሆነው በቀሩ” ብላችሁ አለተመኛችሁም?
አባ ገዳዎችስ የት ነው የምትኖሩት? ይሄ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም እንዴት ነው ወጥታችሁ “ተዉ ልጆች ተገቢ አይደለም፣ በእኛእሬሳ ላይ“ ያላላችሁት? ከመንግሥት ጋር በመናበብ ለሚዲያና ለካሜሪ ብቻ ነው እንዴ የምትወጡት?
የእኛን ልጆች አይወክሉም፤ ቄሮን አይወክሉም፤ ከአጠቃላይ ከኦሮሞ ወጣት ቁጥር አንፃር ሲታይ ይህ የጥፋት ሠራዊት ቁጥሩ በጣም አነስተኛ ነው፤ አናውቃቸውም፤ ከሌላ አካባቢ ነው የሚመጡት፤ …እያላችሁም የተለመደና የማይታመን ምክንያት ድርደራ ውስም አትግቡ፡፡ አያስፈልግም፡፡ እኛም ድፍን ኦሮሞ ወጥቶ ይህን ነውረኛ ድርጊት ፈፀመ አላልንም፡፡ በእርግጥ በድርጊቱ የሚሳተፉት ወጣቶችና ጎልማሶች አገር ለማሸበርም ቁጥራቸው ከበቂ በላይ ነው፡፡ ይልቁንስ ነገር ማለባበሱንና የቁጥርና የመጠን ጨዋታውን ትተን ሀቁን እንጋፈጥ፡፡ አጥፊዎቹ የእናንተው ልጆች፣ የእኛም እህትና ወንድሞች ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አለቀ፡፡
በእርግጥ የጽሁፌ ዓላማ የልጆቻችሁን ሀጥያት በመዘርዘር እናንተን ለማሳጣትና ለማሳቀቅ ሳይሆን መፍትሄውም እናንተ ጋር እንደሆነ ለመጠቆም ነው፡፡
ለአንድ ልጅ እድገት ቤተሰብ፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ያደጉበት ማህበረሰብ እንደአጠቃላይ የየራሳቸው ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ የሐይማኖት ተቋማት የሚለውን ብዙ ነገር ስለሚያማዝዝ ለጊዜው ባልነካካው መርጣለው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱን በተመለከተ ግን ሁሉንም ተማሪ በእኩል የበደለው ስለመሆኑ ብዙ ተብሏልና መድገም አያስፈልገኝም፡፡ ሌላው ተጠያቂ መንግሥት ነው፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ እኛ ኢትዮጵያውያን መንግሥት አይዋጣልንም፡፡ ሁሉ ጊዜ ትሻልን ትተን ትብስን ስናገባ ነው የምንገኘው፡፡ አሁንማ በትብስም ከተገላገልን ጥሩ ነው፡፡ ገና በሁለት አመት ከመንፈቋ ትባባስም አንሷታል፡፡ ሲጀመር ኢ.ህ.አዴ.ግ ማለት በኢትዮጵያ ላይ የመጣ አንዳች ምጣት እንደሆነ ከእናንተ የተሸሸገ አይደለም፡፡ የበኩር ልጁ የሆነው ብልጽግናም ቁርጥ እሱን ነው፡፡ እንደውም ለእናንተ ትንሽ ልቡ ይራራል ልበል!?
ሕግ ያለው አዲስ አበባ ላይ ብቻ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አድራጊ ፈጣሪነታቸው እዚችው እቴጌ ጣይቱ የቆረቆርዋት ከተማ ላይ ነው፡፡ እሳቸውን እንቅልፍ የሚነሳቸው ጉዳይ የአዲስ አበባ ሕዝብ ለመብቱ መደራጀቱ እንጂ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው መብት አልባ ሆነው በዘርና በኃይማኖት መጨፍጨፋቸው አይደለም፡፡ የእሳቸው ነገር እንኳን ተከድኖ ይብሰል ብለን ማለፍ ነው የሚሻለው፡፡ ሰውየው ከዋና ከተማዋ ውጪ አቅምም አቋምም እንደሌላቸው ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ላይ ልጃችሁን ጀዋርን አስፈራርተው፣ እናንተ ክልል ሲመጡ ደግሞ ያን ለማስተባበል ሲኮለታተፉ ሳትታዘብዋቸው አትቀሩም፡፡ እና በአጭሩ ሰውየው የኢትዮጵያ ሳይሆኑ የአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው (ይህ ያንሳቸዋል የሚል ካለ ያልተዋጣለት ቲያትረኛ የሚል ማዕረግ ሊመርቅላቸው ይችላል)፡፡ ስለዚህ እሳቸው ከሚመሩት መንግሥት ይሄነው የሚባል መፍትሄ መጠበቅ ጅልነት ይመስለኛል፡፡
ከዚያ ይልቅ ለጊዜው አቅማችን የሚፈቅደው ቤተሰብ ከዚያም አልፎ ማህበረሰብ የሚለው ላይ ማተኮር ይመስለኛል፡፡ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡ በልጆች አስተዳደግ ላይ ቤተሰብ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ አያጠያይቅም፡፡ አንድ ሥነ-ምግባር የጎደለው ልጅ/ሰው “አሳዳጊ የበደለው” የሚባለው ለዛ ግለሰብ ምግባረ-ብልሹነት የአሳዳጊዎቹ ድርሻ የጎላ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ አይደል? ለዚህ ነው የልጆቻችሁ ሥርዓት-አልበኝነት፣ የጭካኔና የብልግናን ክብረ-ወሰን መስበር፣ በበታችነት ስሜት መወራጨት፣ በፈጠሩት ተሪክ ተጠልፈው መውደቅ ከዛም አልፎ እናንተን ጨዋዎቹን ወላጆቻቸውን ማሰደብ እጅግ አድርጎ ያንገበገበኝ፡፡
ድፍረት አይሁንብኝና ጥቂት ጥያቄዎችን ላንሳ፡፡ የዚህን ሁሉ ችግር ምንጭ ለማወቅ ሙከራ አድርጋችሁ ይሆን? ልጆቻችሁን እንዴት ነው የምታሳድጉት? እነዚህ ዛሬ ሰው ገለው በአስሬን እቃእቃ የሚጫወቱ ልጆች ነገ ለእናንተስ ይመለሳሉ ብላችሁ ታምናላችሁ? መጨረሻቸው እንደማያምር ከወዲሁ አልታያችሁም? ለመሆኑ ትመክሯቸዋላችሁ? ሲያጠፉ ትገስጿቸዋላችሁ? ይሰሟችኋል? ይታዘዝዋችኋል? የጋሞ አባቶች በልጆቻቸው ዘንድ ያላቸውን ከበሬታና ተሰሚነት አይነት እናንተ በልጆቻችሁ ዘንድ አላችሁ? ካላችሁ እሰየው! ከሌላችሁ ግን ለምን ብላችሁ እራሳችሁን መጠየቅ መልካም ይመስለኛል፡፡
መቼስ አብዛኛው የኢትዮጵያ ልጅ በከረሜላ እና በአይስክሬም ሳይሆን በተረት እንደሚያድግ ይታወቃል፡፡ ተረት ደግሞ ዓላማው ማዝናናት ብቻ ሳይሆን በተለይም ማስተማር፤ አእምሮን በመልካም ነገር ማነፅ ነው፡፡ ፈጣሪን ስለመፍራት፣ ከሰው ጋር አብሮ ስለመኖር፣ ስለ አገር ፍቅር፣ ስለሥራ ክቡርነት፣ ስለትምህርት አስፈላጊነት የመሳሰሉት ጉዳዮች በተረት ውስጥ የሚካተቱ ዋና ዋና ጭብጦች መሆናቸውን ለእናንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ስለዚህ ተረቶቻችሁን መለስ ብላችሁ ቃኝዋቸው፤ የዘፈኖቻችሁንም ይዘት ተመልከቱ፤ የልጆች አስተዳደግ ሥርዓታችሁን መርምሩ፤ የግጭት አፈታት ሥርዓታችሁንም ፈትሹት፡
እንደኔ እንደኔ መፍትሄው ያለው እናንተው ጋር ነው፡፡ ግድ የላችሁም ውስጣችሁን ተመልከቱ፡፡ የቱጋር ነው ክፍተት የተፈጠረው? እስቲ ሰብሰብ በሉና ተመካከሩ፤ ተወያዩ፡፡ የአባ መላ ልጆች መላ ፍጠሩ፡፡
እስከዛው ትላንትን አፍቅሬ፣ ዛሬን ጠልቼ፣ ነገን ፈርቼ ምላሻችሁን በጉጉት እጠባበቃለው፡፡
አክባሪያችሁ