ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በወላይታ ዞን ያሉ ሁለት የማኅበረሰብ የራዲዮ ጣቢያዎች አገልግሎትእየሰጡ አለመሆኑ ተገለጸ።
ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ነሀሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን የተከሰተውን አለ መረጋጋት ተከትሎ፣ በዞኑ የሚሰራጩ የማኅበረሰብ ራድዮ ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙ መደረጉን ከዞኑ ነዋሪዎች ማረጋገጥ ተችሏል።
በእለቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች ዞኑን በክልል ለማደራጀት ከተቋቋመው ሴክሬታሪያት ጋር ስብሰባ ላይ ባሉበት ወቅት በጸጥታ ኃይሎች መያዛቸውን ተከትሎ በክልሉ የተፈጠረው አለመረጋጋት አሁን ላይ የረገበ ቢመሰልም በተለያዮ የዞኑ ከተሞች የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ተከትሎ ሕዝቡ በከፍተኛ ቁጭትና ቁጣ ውስጥ እንደሚገኝ እየተነገረ ነው።
ከኹከትና ግርግሩ በኋላ በወላይታ ዞን የሚገኙት የፋና 99 ነጥብ 9 እና የዎጌታ 96 ነጥብ 6 የራዲያ ጣቢያዎች ከእሁድ ነሐሴ 04/2012 ዓ.ም ከጠዋቱ ሦሥት ሰዐት ጀምሮ መረጃ እየሰጡ አለመሆናቸው ታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በስልክ ለኢትዮጵያ ነገ እንደዚህ ረጋገጡት ከሆነ የደቡብ ክልል መንግሥትና የወላይታ ዞን ከፍተኛ ሓላፊዎች በሰጡት ትእዛዝ መሠረት፤ ከሰኞ እለት ማለዳ ጀምሮ ሁለቱም ኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች ቀደሚ ውሳኔውን የሚሽር ትእዛዝ እስኪመጣ ድረስ በመሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ ብቻ እያስደመጡ ናቸው።
እነዚህ የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ ምንጮች ጣቢያዎቹ መረጃ ለመስጠት የተገደዱት በእነዚህ ባለሥልጣናት ትእዛዝ የማኅበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎቹ ሠራተኛ የሆኑ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች በመታሰራቸው እንደሆነም በተጨማሪነት ጠቁመዋል።