ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ለሁለት ቀናት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያካሄደውን ስብሰባ ያጠናቀቀው የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ እጅግ የወረደና አሳፋሪ ንግግር ባደረጉት በአቶ ሽመልስ አብዲሳ ሀሳብ ላይ መወያየቱን ይፋ አደረገ።
በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ቀደም ባላ ጊዜ አደርገውታል በተባለ ንግግር ዙሪያ በኮንፈረንሱ ላይ ውይይት መደረጉን የጠቆሙት የአማራ ክልል የብልፅግና ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ አገኘሁ፤ “አንደኛ ጉዳዩ የተነገረው መቼም ይሁን መቼ፣ ለምን አሁን ማውጣት አስፈለገ? የሚለው አነጋግሮናል። ሁለተኛ ንግግሩ በይዘቱ ስህተት መሆኑን ጭምር” ሲሉ በጉባዔው መጠናቀቂያ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
” በርዕሰ መስተዳደሩ ንግግር ላይ የተንጸባረቀው ሀሳብ የግለሰብ አቋም ነው። የፓርቲያችን የብልጽግና አቋም አይደለም” ያሉት ሓላፊው፤ በውይይቱ የንግግሩ ይዘት በብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ በዝርዝር መገምገም እንዳለበትና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ መቀመጡንም ይፋ አድርገዋል።
“ኮንፈረንሱ የተሰጠው መግለጫ ትክክል አለመሆኑን፣ በይዘት ደረጃ ስህተት መሆኑን ገምግሟል። የይቅርታ መጠየቅ የግለሰብ ጉዳይ ነው። የፓርቲ አቋም ግን አይደለም” ሲሉ ደግመው ደጋግመው ነገሮችን የሚያለዝብ አስተያየት የሰጡት አቶ አገኘሁ፤ በክልሉ የአመራር መከፋፈል አለመኖሩን ፣ አንድነቱ የጠነከረና ለአማራ ሕዝብ እየሠራ ያለ አመራር መኖሩንም አብራርተዋል።
የትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ ወስኖ መንቀሳቀሱ ፀረ ሕገ መንግሥት እንቅስቃሴ ነው ያሉት አቶ አገኘሁ “ሕገወጥ ምርጫ በመሆኑ ፌደራል መንግሥት እርምጃ ይውሰድ ነው የእኛ አቋም” ብለዋል።
“የአማራ ክልል የትግራይ ክልልን ለምን ምርጫ ታካሂዳለህ ማለት አይችልም። የፌደሬሽን ምክር ቤትና ምርጫ ቦርድ እውቅና ስለነፈገው የፌደራል መንግሥት ማድረግ የሚችለውን ያደርጋል።” በማለት ስለቀጣዮ የትግራይ ክልል ምርጫ የክልላቸውን አቋም ይፋ ያደረጉት የብልፅግና ፓርቲ አመራር፤ የራያና ወልቃይት ሕዝቦች አማራ ማንነት ያላቸው በመሆኑ ምርጫወንም አልደገፉትም። ባለመደገፋቸውም በአሁኑ ሰዐት እየታሰሩና እየተሰደዱ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።