በርካታ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ተጠርጥረው የመን ውስጥ በሁቲ ታጣቂዎች ተገደሉ

በርካታ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ተጠርጥረው የመን ውስጥ በሁቲ ታጣቂዎች ተገደሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የሁቲ ታጣቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ በሺኅዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ከሰሜናዊ የመን ማሰወጣታቸውና መግደላቸው ተነገረ።

 ሂዩማን ራይተስ ዎች ያወጣው መግለጫ  ወደ ሳዑዲ ድንበር የተባረሩት ስደተኞች በድንበሩ ጠባቂዎች ሌላ ጥቃት ተሰንዝሮባቸው፤ የተወሰኑ ሰዎች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩት ወደ ተራራማ አካባቢ ለመሸሽ መገደዳቸውን ያሳያል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ድምፃቸውን ለመብት ተሟጋቹ ድርጅት የሰጡ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ለቀናት ያለምግብና ውሃ እንደቆዩ እና በቀጣይም ወደ ሳዑዲ መግባት ቢችሉም ንፅሕና በሌለው ሥፍራ ታጉረው እንዲቀመጡ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አሁንም በየመንና ሳዑዲ ተራራማ ድንበር አካባቢ ሊኖሩ ይችላሉ ሲል ግምቱን ያስቀመጠው ዓለም ዐቀፉ ሂዮማን ራይትስ ዎች ጥናት ቡድን አባላት የሆኑት ናዲያ ሃርድማና የተባሉት ግለሰብ፤ የሳዑዲና የየመን ኃይሎች ኢትዮጵያዊኑ ላይ የፈፀሙትን ግፍ ወቅሰው የተባበሩት መንግሥታት ለጉዳዩ መፍትኄ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ድርጅቱ ሰኔና ሐምሌ ወር ላይ 19 ኢትዮጵያውያንን (13 ወንዶች፣ 4 ሴቶችና ሁለት ታዳጊ ሴቶች ) ፤ ከመስከረም 2014 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ የየመን ዋና ከተማ ሰንዓን የተቆጣጠሩት የሁቲ አማፅያን በሺኅዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን “አል ጋር” በሚባል ሥፍራ ከብበው ጥቃት እንዳደረሱባቸው ድርጅቱ ከጉዳቱ ሰለባ ሰዎች መረጃ ማግኘቱን አስታውቀዋል።
ይህ አሳዛኝ ጥቃት የደረሰው ወርሃ ሚያዚያ ላይ ሲሆን፣ ከዚያም ስደተኞቹን የጭነት መኪና ላይ አሳፍረው ወደ ሳዑዲ ድንበር እንደወሰዷቸውና ሊያመልጡ የሞከሩ ሰዎች ላይ እንደተኮሱ ሂዩማን ራይትስ ዎች ይፋ አድርጓል።
የድርጅቱ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ታጣቂዎቹ ስደተኞቹ ኮሮና ቫይረስ ሊኖርባቸው ይችላል በሚል ከአል ጋር እንዳባረሯቸው  ተገምቷል።
” ታጣቂዎቹ ሥፍራውን ለቀን እንድንወጣ ሲያዋክቡን ነበር ፣ በዚህም መካከል 40 ያክል ሰዎች እንደሞቱ ማየት ችያለሁ” አንዲት የዓይን ምስክር ለሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ገልጻለች። ለድርጅቱ ቃላቸውን ከሰጡ 19 ሰዎች መካከል 12 ሰዎች፤ ስደተኞች ሲገደሉ የተመለከቱ ቢሆንም የሟቾች ቁጥር በይፋ ምን ያክል እንደሆነ ማወቅ ገና እየተጣራ ይገኛል።
አል ጋር የተሰኘው ኢ-መደበኛ የስደተኞች ጣቢያ በርካቶች ተጠልለው የሚኖሩበት ሲሆን፤ ሂዩማን ራይትስ ዎች ጥቃቱ ተፈፅሟል ከተባለበት ወቅት በፊትና በኋላ ያሉ የሳተላይት ምስሎችን ተመልክቶ ቢያንስ 300 መጠለያ ሸራዎች ከጥቅም ውጭ እንደሆኑ አረጋግጫለሁ ብሏል።

LEAVE A REPLY