በደሴ ማረሚያ ቤት ውስጥ 13 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ታወቀ

በደሴ ማረሚያ ቤት ውስጥ 13 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ታወቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በደሴ ማረሚያ ቤት በተደረገ የኮቪድ-19 ምርመራ 13 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋገጠ።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው መሀል 12ቱ የህግ ታራሚዎች ሲሆኑ፣ አንደኛው ግለሰብ ደግሞ የማረሚያ ቤቱ ባልደረባ የሆነ ፖሊስ መሆኑ ታውቋል።
የከተማው ጤና ቢሮና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ከማረሚያ ቤቱ ጋር በመነጋገር፣ አዲስ የሚገቡ ታራሚዎች ለ14 ቀናት ለብቻቸው እንዲቆዩ ከማድረግ በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ ምርመራ ሲደረግላቸው መቆየቱ ተሰምቷል።
ከሐምሌ 20 በኋላ ማረሚያ ቤቱ የገቡ 46 ታራሚዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 10 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ከመሆኑ ባሻገር፤ ታራሚዎቹ ከተለያዩ  ከደቡብ ወሎ ወረዳዎች እና ከደሴ ከተማ የመጡ መሆናቸውን የማረሚያ ቤቱ ሓላፊ አብራርተዋል።
በሁለተኛ ዙር 60 ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ ሦስቱ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል። በሁለተኛው ዙር ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል በመጀመሪያው ዙር እንዳለባቸው ከታወቁ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው እንደሆኑም ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ የተገኘባቸው ቦሩ ሜዳ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የተላኩ ሲሆን፤ ተጓዳኝ ህመም ያለበት አንድ ታራሚ ካሳየው የህመም ምልክት ውጭ ሁሉም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።

LEAVE A REPLY