ከቡራዮ ለይቶ ማቆያ ያመለጡትና በኮሮና የተያዙት ወጣቶች በፖሊስ እየተፈለጉ ነው

ከቡራዮ ለይቶ ማቆያ ያመለጡትና በኮሮና የተያዙት ወጣቶች በፖሊስ እየተፈለጉ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ የቦራ ወረዳ የሕግ ታራሚና በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሁለት ወጣቶች በድጋሚ ከሕክምና ማዕከል መጥፋታቸው ተረጋገጠ።

የሕግ ታራሚዎቹ ቡራዩ ወደሚገኘው የኮቪድ-19 የሕክምና ማዕከል ከተወሰዱ በኋላ ነበር ከሕክምና ማዕከሉ ለሁለተኛ ጊዜ ያመለጡት።  ይህን ተከትሎም በቫይረሱ ተጠይዘው ሕክምና በማቋረጥ የጠፉትን ግለሰቦች ፖሊስ እየፈለጋቸው ቢሆንም እስካሁን አልተገኙም።
በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦረ ወረዳ በሚገኝ እስር ቤት  ውስጥ እያሉ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠው ሻሎ ፊታላ እና ኢሳቾ አበበ የተባሉት ሁለት ወጣቶች፣ እንዲሁም ሌሎች 3 ታራሚዎች ፤ ለሕክምና ወደ ቡራዩ ከተማ መወሰዳቸውን ያስታወሱት የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሚሊዮን ታፈሰ፤  ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው ሁለቱ ወጣቶች፣ ወደ ቡራዩ በተወሰዱ በጥቂት ቀናቶች ውስጥ ከለይቶ ሕክምና ማዕከሉ አምልጠው እንደተሰወሩ ተናግረዋል።
ከሕክምና መስጫ (ለይቶ ማቆያ) ማዕከሉ ያመለጡት ሁለቱ ወጣቶች ከዛ ከወጡ ወደ በኋላ  ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙበት መኖሪያ ቀዬ እንደተመለሱ የሚያሳይ መረጃ መገኘቱንም ኢንስፔክተሩ አስታውቀዋል።
“ወጣቶቹ ከሕክምና መስጫው አምልጠው ወደ ወረዳችን ነው የመጡት፤ በደረሰን ጥቆማ መሠረት ሕዝቡን አስተባብረን አንድ የገጠር መንደር ውስጥ ከያዝናቸው በኋላ ወደ ቡራዩ መልሰናቸዋል” ያሉት ሓላፊው፤ ወጣቶቹ ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከሉ እንዲመለሱ ከተደረጉ ከአራት ቀናት በኋላ ማለትም ቅዳሜ ነሐሴ 2 ለሁለተኛ ጊዜ ከማዕከሉ ማምለጣቸውን እና እስካሁን ድረስም መሰወራቸውን ይፋ አድርገዋል።
“ግለሰቦቹ ለሁለተኛ ጊዜ ማምለጣቸውን ከሰማን በኋላ ፍለጋችንን አጠናክረን እየሠራን ነው። ቤተሰቦቻቸው ጋር የሉም፤ ገጠር ድረስ የኅብረተሰብ ክፍል መረጃ አድርሰናል። እስካሁን ግን አላገኘናቸውም። ምናልባት ወደ ሌላ ወረዳዎች ውስጥ ሳይደበቁ አይቀርም” የሚሉት ኢንስፔክተሩ፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ለማዋል  ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከለይቶ ማከሚያ ማዕከል ያመለጡት ወጣቶች ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረም የቦራ ወረዳ ምክትል የጤና ቢሮ ሓላፊ ወ/ሮ ፍጹም ወርቅነህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY