ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስታራቂ፣ አስተማሪና የሚያቀራርቡ ንግግሮቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጧቸው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ጠየቀ።
አሁን ያለውን ውጥረት ለማርገብ አስፈላጊ ከሆነም የአፍሪካ ሕብረት ወይም የአፍሪካ መሪዎች በማሸማገሉ በኩል ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚችሉና በተለይም የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የደቡብ አፍሪካ ፕ/ት ሲሪል ራማፎሳ ቁልፍ ሚና የላቀ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ቡድኑ ገልጿል።
ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ፣ የትግራይንና የማዕከላዊውን መንግሥት ፍጥጫ ትኩረት ሰጥቶ በገመገመበት ዝርዝር ሪፖርቱ፣ በኦሮሚያ ክልል የሰላም መደፍረስና የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳደር ጋር የገባበት ፍጥጫ በንግግር ሊፈታ እንደሚገባም ጠቁሟል።
ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ብዙዎች ተስፋ የጣሉበት ፖለቲካዊ ሽግግሩ እንቅፋት ሊገጥመው እንደሚችልም ስጋቱን ጠቁሞ፤ በኦሮሚያ ከተሞች በቅርቡ የታዩት ሰላም መደፍረሶች ኢትዮጵያ የጀመረችውን ፖለቲካዊ ሽግግር አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችል አሳሳቢ ቀይ መብራቶች ናቸው ብሏል ድርጅቱ።
የትግራይ ክልል ልሂቃን ክልላዊ ራስን የማስተዳደር መብት በክልልላችን ምርጫ ማካሄድ ሙሉ መብት ያጎናጽፈናል የሚል አቋም እንደያዙ፣ የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ ሕገ መንግሥቱ ይህን እንደማይፈቅድ በማሳወቁ ፍጥጫው የበረታ በመሆኑ ሁለቱም ወገኖች ከዚህ በመነሳት ፖለቲካዊ ጡዘቶችን እንዲያረግቡ አሳስቧል።
ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ማዕከላዊ መንግሥት በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ላይ ጫና ለማሳደር እየሞከረ ነው ባለበት ሰሞነኛ አዲስ መግለጫው፤ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ በበኩሉ ምርጫ አካሄዳለው በሚል እየዛተ ነው ሲል የጉዳዮን መካረር ከመጠቆሙ ባሻገር፤ ሁለቱም የያዙት አቋም እንደማያዋጣ ይፋ አድርጓል።
አሁን ላይ ሁለቱም የገደል ጫፍ ላይ ናቸው ያለው ድርጅቱ በብልጽግናና በህወሓት መካከል ያለው መጠላላትና ሽኩቻ በመጨረሻ የአገር ተስፋን የሚያጨልም ሊሆን እንደሚችልም አስረድቷል።