ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከእሁድ ጀምሮ ለተፈጠረው ኹከትና የተቃውሞ ሰልፍ እጃቸው አለበት የተባሉት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳጋቶ ኩምቤን ጨምሮ ፤ እሑድ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ የዞኑ ባለሥልጣናትና የማኅበረሰብ መሪዎች ትናንት ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የወላይታ ዞን አደራጅ የሆኑት እነዚህ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎችና ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ትናንት በቦዲቲ ከተማ የቀጠለ ሲሆን አሁንም በአንዳንድ ሥፍራዎች የአመፅ ስሜቱ እንዳልበረደ እየተነገረ ነው።
የዞኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የወላይታ ልሂቃን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ባለፈው እሑድ ነሐሴ 3 ቀን ሶዶ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ጉተራ አዳራሽ ስብሰባ በማድረግ ላይ ሆነው ነበር በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
ከእነዚህ የኅብረተሰቡ ተወካዮችና ባለሥልጣናት መካከል ትናንት ከሰዐት በኋላ በወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች ናቸው። በዝግ ችሎት የተካሄደው የፍርድ ቤቱ ውሎ እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዐት ገደማ ድረስ ከተካሄደ በኋላ፣ ለዛሬ 9፡00 ሰዐት ተቀጥረው ነበር። ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዐት ድረስ ችሎቱን የተመለከቱ መረጃዎች አልወጡም።
ከሁለት ቀን በፊት 28 የዞኑ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በአጠቃላይ 178 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማረጋገጡ ተሰምቷል።