ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከጃል ዳውድ ኢብሳ እውቅና ወጪ ሲንቀሳቀስ የቆየውና የፓርቲው ሊቀመንበር በሌሉበት ድርጅታዊ መግለጫዎችን ሲሰጥ የሰነበተው በአራርሳ ቢቂላ የሚመራው ቡድን የኦነግ ሊቀመንበርን ከሓላፊነት ማገዱን ገለጸ።
የሥራ አስፈፃሚ ቡድኑ ከሁለት ሳምንት በፊት አንስቶ በኦነግ አመራሮች ውስጥ ሲካሄድ የቆየውን ውስጣዊ ሽኩቻ ሲሸፋፍን የቆየውና አዲሰ ቡድን የፈጠረው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮማቴ የኦነግ ሊቀመንበር ከሓላፊነታቸው እንዳልተነሱ ሲናገር ቢቆይም ዛሬ ግን የበረሃው የድርጅቱ መሪ ከኦነግ ሊቀመንበርነት በጊዜያዊነት ማገዱን ይፋ አድርጓል።
ጃል ዳውድ ኢብሳ በኦነግ ቤት ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ፈጽሞ ያልገባቸው መሆኑን፣ እየተደረገ ያለው ድርጅታዊ እንቅስቃሴ ከእርሳቸው እውቅና ውጪ ከመሆኑ ባሻገር፤ መንግሥት ኦነግ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት በመፍራት በድርጅቱ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ግንባሩን የመከፋፈልና የመበታተን ሥራ እየሠራ ነው ሲሉ መናገራቸውን ኢትዮጵያ ነገ ከቀናት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።
በሳምንቱ መጀመርያ የኦነግ ሊቀመንበር (ዳውድ ኢብሳ) ባልተገኙበት በሂልተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ምክትል ሊቀመንበር አራርሳ ቢቂላ ከዳውድ ኢብሳ ጋር የሚገናኙበት ሁለቱም የእጅ ስልክ የማይሠራ በመሆኑ ግንኙነታቸው መቆሙን ለሸገር ራዲዮ የተናገሩ ሲሆን፤ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለጊዜው ጃል ዳውድ ኢብሳን ከኦነግ ሊቀመንበርነት ማገዱን አስታውቀዋል።