ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአዋሽ ወንዝ በከፍተኛ ሁኔታ በመሙላቱ መኖሪያ ቤቶችና አካባቢውን በማጥለቅለቁ 500 አባዎራዎች መፈናቀላቸውን የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ድሪብሳ ዋቁማ አስታወቁ።
የጎርፍ አደጋው ከደረሰበት ሰዐት አንስቶ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ የተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ወጤታማ እንደነበር ያስታወሱት ሓላፊው፤ ጀልባዎችን ከተለያዩ ሦፍራዎች በማስመጣት የሰዎችን ሕይወት መታደግና ንብረታቸው ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ አሁንም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
“በጎርፍ አደጋው አምስት መቶ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ለእነርሱም የጊዜያዊ መጠለያ አዘጋጅተናል። እንዲሁም የቤት እንስሳቶቻቸው በጎርፉ እንዳይጎዱ የማዳንና ሳር የማቅረብ ሥራም እየሠራን እንገኛለን ” ያሉ የምእራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ፤ የደረሰው የጎርፍ አደጋ ከሚገመተው በላይ ቢሆንም ፣ ለችግር የተጋለጡትን ማህበረሰቦች እንዲያገግሙ ለማድረግ ከዞኑ አቅም በላይ እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝብለዋል።
የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በምዕራብ ደቡብ ሸዋ ዞን በኢሉ ወረዳ ከ 7 ሺኅ 900 በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል።
ዘንድሮም በተመሳሳይ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀሬ ወረዳ ዲቡ ቀበሌ ወንዙ ሞልቶ በመፍሰሱ የተነሳ፣ ቀበሌው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ጉዳት እንደደረሰበት የቀበሌው አስተዳደር አቶ ከበደ ዲሳሳ ገልጸዋል።
በጎርፉ አደጋ ቀያቸውን ጥለው በመጠለያ እየኖሩ ከሚገኙት በርካታ ሰዎች መሀል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ጌጤ ቦርጋ፣ “ዘንድሮ በአገሪቱ ያልነበረ አደጋ ነው የመጣብን፤
ከምሽቱ ሦስት ሰዐት ነው ደራሽ ውሃው የመጣብን፤ ከሁለት ልጆቼና ከባለቤቴ ጋር ቤት ውስጥ ነበርን፤ ባለቤቴ አይነ ስውር ናቸው። ጎረቤት ነው ደርሶ ግድግዳ በመብሳት እንድንቆይበት ቆጥ የሠራልን፤ መያዝ የምንችለውን ይዘን እዚያው ቆጥ ላይ ነው የቆየነው” በማለት አሳዛኙን ክስተት ገልጸውታል።
አሁን ላይ መጠለያ ቢገቡም እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ላለፉት ሦስት ቀናት ግን የውሃው መጠን መቀነስ ስላልቻለ፣ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እዚያው ቆጥ ላይ ማሳለፋቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ጌጤ ፤ ከሦስት ቀን በኋላ ግን ጀልባ ደርሶላቸው ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ስፍራ እንደተወሰዱ ይፋ አድርገዋል።
ሌሎች በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ጎርፉ ቤት መጠለያቸውን ማፍረሱን ተከትሎ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ለሦስትና አራት ቀናት በዛፎች ላይ ተንጠላጥለው ፈታኝ ቀንና ሌሊቶችን ማሳለፋቸውም ተሰምቷል።