ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በቴፒ የተነሳውን ኹከት ተከትሎ የመንግሥትና የግል ተቋማት ከተዘጉ አምስት ቀን እንዳለፋቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች እንዳስረዱት ከተማዋ ከተለያዩ አካባቢዎች የምትገናኝበት የትራንስፖርት አገልግሎት ከተቋረጠም ዓመት እንዳለፈው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህንን የተቋረጠውን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሰቀጠል በማሰብ፣ የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መኪኖች ያሏቸው የከተማዋ ነዋሪዎችን ቢያስገድድም አለመሳካቱን ተከትሎ በፀጥታ ኃይል በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መረዳት ተችሏል።
“ለንግድ ቤቶቹ መዘጋት ምክንያቱ ከቴፒ ማሻና ጌጫ የሚወስደውን መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት በግዴታ ለማስጀመር የአካባቢው አስተዳደር ሲሞክር ባለመቻሉና ባለቤቶቹ በመታሰራቸው ነው” ያሉት የቴፒ ነዋሪዎች፤
የትራንስፖርት አገልግሎት በግድ ለማስጀመር በማሰብ አሽከርካሪዎችንና የተሽከርካሪ ባለቤቶች በመታሠራቸው ኅብረተሰቡ የንግድ ተቋማትን ዘግቶ መቀመጡም ይፋ አድርገዋል።
“በአካባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ንግድ ቤቶች እንዳይከፈቱ በማዘዛቸው የተነሳ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እስከ ንግድ ድርጅቶች ያሉ ተቋማት ከተዘጉ አምስት ቀናት አልፏቸዋል” የሚሉት በቴፒ “ኩቢቶ” በተሰኘ አካባቢ የሚኖሩ ግለሰብ የከተማው ሕዝብ ያነሳውን የመዋቅር ጥያቄ አስመልክቶ እስካሁን ሳይመለስ መቆየቱ የፈጠረው ቅሬታ ወደ ተቃውሞ ተሸጋግሯል ብለዋል።
እስካሁን ድረስ በአካባቢው የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት እንደማይሠሩ፣ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሌለ ያረጋገጡት ነዋሪዎች፤ የተነሳውን ብጥብጥና ግድያ ተከትሎ ወጣቶች ጫካ መግባታቸውንም ጠቁመዋል።
በአንጻሩ “ታጣቂዎች አላዘጉንም፤ ማንም ዝጋ ብሎ ያዘጋው የለም፤ ኅብረተሰቡ ለራሱ ደህንንት ፈርቶ ነው የዘጋው” ሲሉ የኹከቱን መነሻ አስመልክቶ ለቢቢሲ ሀሳባቸውን የሰጡ የቴፒ ነዋሪዎችም አሉ።
አካባቢው አሁን የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን የገለጹት የደቡብ ክልል ፖሊስ ልዮ ኃይል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር እንዳለ አበራ፤ “ችግር የሚፈጥሩት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሽፍቶች ናቸው። መንገድ ላይ መኪና በማስቆም ይዘርፋሉ፤ ኅብረተሰቡን በየቤቱ በመሄድ ገንዘብ አምጣ በማለት ይዘርፋሉ፤ እምቢ ካሉም ይገላሉ” ሲሉም የችግሩን ጥልቀት አሳይተዋል።
ነዋሪዎች ጫካ ገቡ የሚባሉት ወጣቶች መሳሪያ መታጠቃቸውን ሲናገሩ፣ ኮሚሽነሩ በበኩላቸው ኅብረተሰቡ ሰላም ወዳድ ነው ብለዋል።