ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– መስከረም ወር ላይ እምቦጭ አረምን ለማስወገድ የሚያስችል የዘመቻ ሥራ ይከናወናል ተባለ።
የተረሳውና የጣና ሐይቅን የወረረው እምቦጭ አረምን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ በተዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት ዛሬ ምክክር ተደርጎበታል።
የተነደፈው ስትራቴጂክ ዕቅድ አረሙን ማስወገድ፣ በዘላቂነት የውኃና አካባቢ ጥበቃ መሥራት፣ ነፃ የሐይቅ ዳርቻ መሥራትና እንዲሁም በሐይቁ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑም ታውቋል።
በዕቅዱ ላይ ሠፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ የእምቦጭ አረም በ1956 ዓ.ም በአባ ሣሙዔል ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ መጤ ወራሪ አረም መሆኑን ጠቁመው፣ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በጣና ሐይቅ ላይ አረሙ በፍጥነት ተስፋፍቶ በአማራ ክልል በሚገኙ ሠባት ወረዳዎችና 35 ቀበሌዎች መዳረሱን ጭምር ይፋ አድርገዋል።
እምቦጭ አረም በብዝኃ ሕይወት አንዲሁም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የደቀነው ሥጋት ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ በቀጣይ ችግሩን ለማስወገድ በሠፊው እንደሚሠራ ዶክተር ስለሺ አብራርተዋል።
በጣና ሀይቅና በአጠቃላይ በጣና ተፋፈስ ዙሪያ የእርሻ መስፋፋት፣ የውኃ አካላት ላይ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ ከከተማና ከኢንዱስትሪ ወደ ጣና ሀይቅ የሚገቡ ፍሳሾች አረሙ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እያደረጉ ቢሆንም፣
ይሁንና አረሙን ማስወገድ የሚቻለው ልማዳዊ ከሆነ አሠራር ወጥቶ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚገባም በምክክር መድረኩ ተገልጿል።