እውን እንደ ስምህ፣
ቢሆንማ ግብርህ፣
አገርን ከጠላት፣
ወገንን ከጥቃት፣
መከላከል ነበር፤ የጀግንነት ስራ፣
ዘወትር ስምህን በክብር የሚያስጠራ፤
…መብት ጠያቂዎችን፣
ንጹሃን ዜጎችን፣
እጃቸውን አጣምረው፣
ባዶአቸውን ቆመው፣
አልሞ መረሸን…
አረመኔ ተግባር የፈሪ ዱላ ነው!!
እስኪ ልባም ከሆንክ፣ ለአገር አሳቢ፣
የትውልድን ጋሻ ወራሽ ተረካቢ፣
ከጨካኝ አርዮሶች፣ ከሰው ልጅ አራጆች፣
በዘር ሳትወግን ከከንቱ ከንቱዎች…፣
ንጹሃንን ታደግ፤ ሁናቸው ከለላ፣
ፊትህን አዙረህ፣ በ’አውሬ’ ሳታስበላ!!
ነሐሴ 2012 ዓ/ም
(ኦገስት 2020)
*በዘርና በቋንቋ የምትሸነሸን ኢትዮጵያ፣ ህልውናዋና መፃዒ ዕድሏ፣ እንደ ዜጋ የሚያሳስበኝና በግሌ ሃሳቡን የማልደግፍ ብሆንም፣ በአገሪቱ ህግ ቦይ ተቀዶለት ለሌሎች በተተገበረበት ሁኔታ፣ “ማን ከማን ያንሳል” ብለው የድርሻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመጠየቅ በተነሱ የወላይታ ወገኖቼ ላይ የተፈጸመውን አስነዋሪ ግድያና ግፍ በመቃወም።