ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ማኅበረሰብ ዐቀፍ የኮቪድ 19 ምርመራ ዘመቻ ለማካሄድ የሚያገለግሉ የተለያዩ ግብዓቶችን አሠራጭቻለሁ አለ።
ኤጀንሲው በ8 ቅርንጫፎችና በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት አማካኝነት ለምርመራ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ማሠራጨቱን የኢጀንሲው የመድኃኒትና ሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ሥርጭት ቡድን መሪ አቶ ተስፋሁን አብሬ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቫይረሱን መስፋፋት ተከትሎ መንግሥት 200,000 ሰዎችን ለመመርመር በያዘው ዕቅድ መሠረት ኤጀንሲውና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ግብዓቶቹን ከነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ማሠራጨቱ የተነገረ ሲሆን፣ ግብዓቶቹ 4 ሚሊየን 955 ሺኅ 646 ብር በላይ ወጪ እንደሀደረገባቸውም ታውቋል።
ሥርጭቱ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ለሲዳማ፣ ለኦሮሚያ፣ ለአማራ፣ ለትግራይ፣ ለሀረሪ፣ ለደቡብ ለቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ለጋምቤላ፣ ለሶማሌ እንዲሁም ለአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮዎች መካሄዱም ይፋ ተደርጓል።