ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞው የኢዴፓና የቅንጅት ከፍተኛ አመራር አቶ ልደቱ አያሌው እጅ ላይ የተገኘው ሁለተኛው ሽጉጥ ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ በተባለ ሰው ስም የተመዘገበ ነው ሲል መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።
ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ በቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ልደቱ አያሌው፤ አቶ ኢሳያስ በወቅቱ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ሓላፊ እንደነበሩ ተናግረው፤ እርሳቸው (አቶ ኢሳያስ) ሓላፊነታቸውን ተጠቅመው እንደሰጧቸው ገልጸዋል።
በእለቱ የችሎት ውሎ መርማሪ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያቀረበው ማስረጃ ግን ተቋሙ ያስታጠቃቸው እንዳልሆነ አረጋግጧል።
ፍርድ ቤቱ በባለፈው ቀጠሮ በሀገር ውስጥ የልብ ሕክምና እንዲያገኙ ማዘዙን ተከትሎ፣ አቶ ልደቱ ላንድ ማርክ ሆስፒታል ክትትል ማድረጋቸውን እና የልብ እና የአስም ሕመምተኛ መሆናቸውን የሕክምና ማስረጃ በጽሑፍ አቅርርበዋል።
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ይህን ተረድቶ ወደ ውጭ ሀገር ተጉዘው እንዲታከሙ እንዲፈቅድላቸው እና የታሰሩበት እስር ቤት ለበሽታ ተጋላጭ ስለሚያደርጋቸው፣ የጤናቸው ሁኔታ አደጋ ውስጥ እንደሆነ በማስረዳት የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ጠይቀዋል።
ልደቱ አያሌው ቀደም ሲል ፍርድ ቤት በቀረቡበት ጊዜ ጥብቅና የሚቆምላቸው ሰው ማጣታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ህገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበር በማሰብ መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ አቁሞላቸዋል።
መርማሪ ፖሊስ አቶ ልደቱ አያሌው ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ በርካታ ምርመራ እየሠራ መሆኑን ጠቁሞ፣ በእጃቸው ላይ የተገኘ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ለፎረንሲክ ምርመራ መላኩን እና ውጤት እየተጠባበቀ ስለሆነም የጀመረውን የምርመራ ሥራ አጠናቆ ለማቅረብ ተጨማሪ የ14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል ።
ፍርድ ቤቱም የተጠርጣሪን የጤናቸውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ምቹ አያያዝ እንዲኖር ለፖሊስ ትእዛዝ ሰጥቶ፤ ሕክምናቸውንም በተገቢው መልኩ በሀገር ውስጥ እንዲከታተሉ ትእዛዝ ከማስተላለፉ ባሻገር፤ መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ተጨማሪ የሠባት ቀን ፍቃድ ሰጥቷልተ