450 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከሊባኖሰ በራሳቸው ወጪ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው

450 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከሊባኖሰ በራሳቸው ወጪ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በሊባኖስ የሚገኙ 450 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃድ ማግኘታቸውን በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ይፋ አደረገ።

ጽሕፈት ቤቱ በሊባኖስ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ዜጎች መረጃዎችን ለአገሪቱ ኢምግሬሽን ጉዳዮች መሥሪያ ቤት አስገብቶ አስፈላጊውን ማጣራት ከተደረገ በኋላ 450 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቃድ መገኘቱን በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ጀነራል ተመስገን ዑመር ተናግረዋል።
ወደ ሀገር ቤት ከሚመለሱት ኢትዮጵያውያን በቤይሩት የወደብ ፍንዳታ ምክንያት በመጠለያ ውስጥ ያሉ እንደሚገኙበት የጠቆሙት ሓላፊው፤ ቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎችን ዝርዘርን በቀጣይ ቀናቶች ውስጥ እንደሚያሳውቅ፣ እንዲሁም የሚመለሱት ዜጎች የትራንስፖርት ወጪያቸውን በራሳቸው የሚሸፍኑ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
በስምንተኛው ዙር የሥም ዝርዝራቸውና መረጃቸው ተልኮ ፈቃድ ያላገኙ ኢትዮጵያውን አሉ ያሉት አቶ ተመስገን፤
በሊባኖስ ሕግ ወንጀል የሠሩ፣ የፍርድ ቤት ጉዳይ ያለባቸው፣ ከአሠሪዎቻቸው ጋር ውል ያልጨረሱና
ሌሎች ምክንያቶች ያሉባቸው  ዜጎች የመመለሻ ፈቃድ እንደማያገኙም አስታውቀዋል።
በሊባኖስ አሁን ካለው አሳሳቢ ሁኔታ አንጻር እነዚህ ዜጎችም ቢሆኑበልዩ ሁኔታ ኢትዮጵያውያኑ ፈቃድ አግኝተው እንዲመለሱ ለኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤቱ ጥያቄ እንደሚቀርብ አመልክተዋል።
ስደተኞቹ ኢትዮጵያውያኑ ለመመለስ ፈቃድ የተሰጣቸው ቢሆንም፤ የመውጫ ቪዛ ለማግኘት ከሁለት እስከ ሦስት ወር የሚፈጅ በመሆኑ በፍጥነት ኢትዮጵያውያኑ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑና ከሦስት መቶ ሺኅ በላይ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት መመዝገባቸውም ታውቋል።

LEAVE A REPLY