ኢትዮጵያ በጥቅምት ወር ሁለተኛ ሳተላይት ለማምጠቅ ማቀዷን አስታወቀች

ኢትዮጵያ በጥቅምት ወር ሁለተኛ ሳተላይት ለማምጠቅ ማቀዷን አስታወቀች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ኢትዮጵያ በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ወራት ሁለተኛ ሳተላይት ወደ ሕዋ ለማምጠቅ ማቀዷን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ የጉዳዮ ዝርዝር መረጃው በቀጣይ ይፋ እንደሚሆን ጠቁመው፤ በ2013 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ናኖ ሳተላይት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሕዋ ለማምጠቅ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሕዋ የምታመጥቀው ሳተላይት ባለፈው ታኅሣሥ ወር ወደ ሕዋ የመጠቀችው ETRSS-1 ሳተላይትን በመጠቀም ማግኘት የማይቻሉ መረጃዎችን ለማግኘት ያግዛል ተብሏል።
ዳግም የሚከናወነው ሳተላይት የማምጠቅ ሥራ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ ወደ ሕዋ ከተላከችው የመጀመሪያዋ ሳተላይት ልምድ በመውሰድ የሚከናወን ከመሆኑ አኳያ ፈተናዎች ቀላል ይሆናሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ታኅሣሥ 2012 ዓ.ም ውስጥ የተላከችው ሳተላይት ከምትልከው ትልቅ የመረጃ ሀብት ማግኘት መቻሉን ጠቁመው፣ በአምስት ወራት ውስጥ ለምርምር ተቋማት እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መረጃ ከሳተላይቷ እንደተገኘም አረጋግጠዋል።
በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዐሥራ አምስት ዓመታት ዐሥር ሳተላይቶች ለማምጠቅ እቅድ መያዟን ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተር መግለጫ መረዳት ተችሏል።

LEAVE A REPLY