ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከነሐሴ 9 እስከ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ለሦስት ቀናት የቆየ አመታዊ 4ኛ ዙር መደበኛ ስብሰባዉን በአዲስ አበባ ከተማ በድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት አካሂዶ አጠናቅቋል፡፡

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዉ በፓርቲዉ ዉስጥ ባሉት የአመራር እና የመዋቅር ጉዳዮች ዙሪያ የተወያየ ሲሆን በወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታዎችና በሕዝባችን ላይ እየተፈጸሙ ባሉ ዘር እና እምነት ተኮር ጥቃቶች እንዲሁም ባንዣበቡ አደጋዎች ዙሪያ ሰፊ ዉይይቶችን አድርጎ በቀጣይ መደረግ ያለባቸዉን ጥናቶች ብሎም ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በመለየት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በአጠቃላይ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለዉይይት ተቀርጸዉ በነበሩ መሠረታዊ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ዉይይት አድርጓል፡፡

በአጀንዳነት ተመዝግበዉና ዉይይት ተደርጎባቸዉ ዉሳኔ ከተሰጠባቸዉ ጉዳዮች መካከል ድርጅታችን ከምስረታው ጀምሮ አጽንኦት ሰጥቶ ከሚታገልላቸዉ እና በፖለቲካ ፕሮግራሙ ዉስጥ በግልጽ ከሰፈሩ መሠረታዊ አጀንዳዎች አንዱ የሆነዉን በሴራ የተቃኘ እና ጊዜያዊ የኃይል ብልጫ አግኝቻሁ በሚል ከአማራ ሕዝብ በመንጠቅና በመነጠል በተለያዩ ክልሎች እንዲካተቱ የተደረጉትን በማንነት፤ በሥነልቦና እና በታሪክ (የ)አማራ አካል የሆኑትን ሕዝቦች እና አካባቢዎች ከሚመስላቸዉ እና አብረዉ መሆን ከሚፈልጉት የአማራ ሕዝብ ጋር ተቀላቅለዉ በአንድ ክልላዊ አስተዳደር ስር መሆን አለባቸዉ የሚለዉ ነዉ።

የሽብር ቡድን ሆኖ ተመስርቶ እና የሽብር መንግስት ሆኖ አሳልፎ በመጨረሻ ወደነበረበት አርከን ተገፍቶ የወረደዉ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር(ትሕነግ) በታሪክ ክፍተት አልፎ ሀገራዊ ስልጣን መቆጣጠር መቻሉን ተከትሎ ካነገባቸዉ ዓላማዎቹ እና ከማደረጃ መርኾዎቹ መካከል አንዱ የአማራን ሕዝብ ዘላቂ የሆነ የማኅበራዊ እረፍት መንሳት ነዉ፡፡ የዚህ እኩይ ዓላማ አካል አድርጎ ተፈጻሚ ያደረገዉ የአማራን ሕዝብ እና አካባቢዎች ወደ ተለያዩ ክልሎች ማካለል ሲሆን ከእነዚህ መካከል የወልቃይት፤ የፀገዴ፤ የፀለምት እና የራያ አማራ ሕዝቦች ተጠቃሽ ናቸዉ።

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) የማዕከላዊውን መንግስት ስልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ በሚኖረው የአማራ ሕዝብ ላይ የተቀነባበሩ የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጽዳት እና ማንነትን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ ጥቃቶችን ሲፈጽም እና ሲያስፈጽም ቆይቷል፡፡ በተለይም ትሕነግ በቀጥታ በሚያስተዳድረዉ የትግራይ ክልል ስር በጉልበት ባካለላቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች ላይ እስከአሁን ድረስ የዘለቁ ዘግናኝ ግፎችን ሲፈጽም ቆይቷል።

የአማራ ሕዝብ ከባድ መስዋዕትነትን በመክፈል ባደረገዉ ትጋድሎ በትሕነግ ይመራ የነበረዉን የማእከላዊ መንግስት አገዛዝ እስትንፋሱን በማቋረጥ አማራ ጠል ራዕዩን ከትቦ ወደተነሳት ሰፈር አሽቀንጥሮ መልሶታል፡፡ በዚህ ረገድ በመላው ሀገራችን ዉስጥ በተለይም በአማራ ሕዝብ በኩል ሲደረግ የነበረዉን የእኩልነት እና የነጻነት ትግል ወደ ልዩ የከፍታ ምእራፍ በማሸጋገር የትሕነግን አገዛዝ ወደ መቃብር ለማውረድ ወሳኝ ድርሻ ያበረከተዉና በኃይል በተካተቱት አካባቢዎች ያሉ አማራዎችን መብቶች ለማስከበር እና የማንነት ጥያቄዎችን ለማስመለስ በግንባር ቀደምነት የተሰለፉ የአማራ ልጀች የፈጸሙት የአርበኝነት ተጋድሎ መሆኑን ግራቀኙ የማይስተው ሃቅ ነዉ፡፡

ሆኖም የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወገኖቹ ጋር በትብብር ባደረገዉ ተጋድሎ ግፈኛውን፣ ከፋፋዩን እና ዘረኛውን የትሕነግ አገዛዝ ከማዕከላዊ መንግስት መንበር አሽቀንጥሮ መጣል እና ማባረር ቢችልም ወደ ትግራይ በኃይል የተካለሉት አሁንም በትሕነግ አገዛዝ በከፍተኛ ጭቆና ስር የሚገኙት የአማራ ሕዝብ ነጻ ያልወጣበት እንቆቅልሽ የግድ መፈታት አለበት፡፡ የትሕነግን የጭቆና ስርዓት በመቋቋም እየተፈጸሙ ያሉትን ዘር-ተኮር ጥቃቶች ቀሪ ለማድረግ በሚል መሪ ምክንያት የመጣዉ አንጻራዊ ሀገራዊ ለዉጥ እና ተከትሎ የተመሰረተዉ “የለዉጥ ስርአት” ለወልቃይት፤ ለፀገዴ፤ ለፀለምት እና ለራያ የአማራ ሕዝብ እስካሁን አንዳች የተሻለ ነገር ማበርከት አልቻለም። ይባስ ብሎም በሀገር ደረጃ ተንሰራፍቶ የነበረዉ የትሕነግ የጭቆና ስርዓት ከማዕከል ተገፍቶ የሄደዉን ኃይሉን ጭምር በአንድ ቀጣና እንዲያሰባስብ መፈቀዱ በተለይ በአካባቢዎቹ የአማራ ወገኖቻችን ላይ የሚፈጸመዉ ግፉ እና ጭቆና እንዲበረታ አድርጓል፡፡

በሀገራችን በተከሰተው የሳንባ ቆልፍ (COVID-19) ወረርሽኝ ምክንያት ክልላዊና ሀገር አቀፉ ምርጫ እንዲሸጋገር የተወሰነ ቢሆንም ትሕነግ ራሱ ቀርጾ ስራ ላይ ያዋለዉን “ሕገ-መንግስት” በግልጽ በሚጥስ መልኩ በትግራይ ክልል ምርጫ ለማድረግ ወስኖ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል። አብን ትሕነግ የቀረጸዉን ሕገ-መንግስት በተመለከተ ያለዉ አቋም ግልጽ እና ያደረ ነዉ፡፡ በርግጥ በትሕነግ ዘመን በተለይ መብቶችን በሚመለከት ያሉት የሕገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች ባለማከበር ሲከበሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ትሕነግ ለማድረግ ያወሰነዉን ምርጫ በሕገ-መንግስቱ የሚደገፍ ለማስመሰል የሄደበት ርቀት እና ፍጹም ለማያዉቀዉ የቅቡል ምርጫ ጉዳይ ጠበቃ ሆኖ መቅረቡ ራሱን ብቸኛ የሕግ ትርጉም እና የፍትኅ ምንጭ አድርጎ ከመዉሰድ ባኅሉ የተቀዳ ሲሆን ድርጅቱ ከእዉቀት፣ ከሞራል እና ከሕግ በቋሚነት የተፋታ ስለመሆኑ ዓብይ ማሳያ ነዉ፡፡

በትሕነግ በኩል ያለዉ የምርጫ አካሂዳለሁ ዉሳኔ በወቅታዊ እና ተጨባጭ የሀገራችን ሁኔታዎች ክህደት ላይ የተመሰረተ፣ አጠቃላይ ግጭት ለመጥራት እና ሀገራችንን ለማፍረስ ያለመ፤ የፌዴራሊዝምን ጽንሰ-ኃሳብ ገሸሽ በማድረግ የተቃኘ እና ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ሲሆን ከመነሻ እሳቤዉ ጭምር ፉርሽ(Void) ነዉ::

ትሕነግ ምርጫውን ለማከናወን መወሰኑን ተከትሎ ከመቸውም ጊዜ በላይ በወልቃይት እና አካባቢዎቹ እንዲሁም በራያ ሕዝብ ላይ ጥቃት እና ጭቆናውን አጠናክሮ በመቀጠል ሕዝቡን ለጅምላ እስር፣ መፈናቀል እና ስደት እየዳረገ ይገኛል። ሕዝቡ ትሕነግ ሊያከናወን ባቀደው የይምሰል ምርጫ ላለመሳተፍ ቢወስኑም የአካባቢዎቹን የአማራ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በዘላቂነት ለመድፈቅ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመቁጠር ምርጫውን በኃይል ለማስፈጸም እየሰራ ይገኛል፡፡

ስለሆነም፦

1. ይህ የትሕነግ እሳቤ፣ ተያያዥ እንቅስቃሴዎች እና በልዩ ሁኔታ የአማራ ማንነትን መሰረት አድርጎ እየፈጸማቸዉ ያሉ ዘርፈብዙ ጥቃቶች ለድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) እና ለመላው የአማራ ሕዝብ እጅግ አሳሳቢ ሆነዋል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው የአማራ ሕዝብ፤ ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ ለአማራ ብሔራዊ ክልል መንግስት እና ለፌዴራል መንግስቱ ሕዝቡ እያደረገ ካለው ትግል ጎን በመቆም ድጋፋቸዉን እንዲሰጡ፤ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የአማራ ሕዝብ ትሕነግ በየዕለቱ የሚፈጽመቻዉን የፀብ አጫሪነት ድርጊቶ እና ትንኮሳ በመመከት አካባቢዉን በንቃት እንዲጠብቁ፡፡

2. በትሕነግ ጥቃትና አፈና ምክንያት ከቀያቸዉ ለተፈናቀሉ ወገኖቻችንም የክልሉ መንግሰትና ሕዝብ ተገቢዉን ድጋፍ እንዲያደርጉ፤

3. የአማራ ሕዝብ ያሉትን የድንበር እና ወሰን ጉዳዮች በተለይም የወልቃይት እና የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄዎች በሕግ አግባብ መፍትኄ እስኪያገኙ ድረስ የማንነት ጥያቄዎቹ ቀርበዉለት ጉዳዮቹን በይደር የያዘው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የእግድ ትዕዛዝ/Injunction/ እንዲሰጥ፤

4. በሕገ-መንግቱ አንቀጽ 13(1)፤ 55 (16)፤ 62(9) ድጋጌዎች እንዲሁም በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 77(10) እና 93 ድንጋጌዎች መሰረት የፌዴራሉ መንግስት፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለዉን ዘግናኝ እና መጠነሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የማስቆም ኃላፊነታቸዉን እንዲወጡ እና ትሕነግ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ወደከፋ እና ተመልሶ ሊካካስ ወደማይችል ደረጃ ከመድረሱ በፊት በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ ጥሪያችንን እስተላልፋለን፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አማራዎችን በሚመለከት ቀደም ሲል ባወጣነዉ መግለጫ የጠየቅናቸዉ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነዉ ከጥቃቱ በሕይወት የተረፉ ወገኖቻችን አሁንም በከፍተኛ ችግር ዉስጥ መሆናቸዉ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊዉን ድጋፍ እንዲያደርግ በድጋሚ እየጠየቅን አሁንም ንጹሀንን በመያዥያነት የሚጠቀሙ ጽንፈኛ የጥላቻ ኃይል በቀጣይ ጥቃቶችን ለመፈጸም ፍላጎት እንዳላቸዉ እና እንደሚዘጋጁ በመገንዘብ በመንግስት በኩል አስተማማኝ የሆነ የደኅንነት ጥበቃ እና የሕግ የበላይነት የማስፈን ተግባራት እንዲያከናዉን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ይጠይቃል፡፡

በሌላ በኩል በአብን በ2012 ዓ.ም 4ኛ ዙር የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ወቅት የተወሰኑ ዉሳኔዎችን አፈጻጸም እንደዚሁም የስራ ክንዉኖችን በተመለከተ በአዎንታዊነት የገመገመ ሲሆን ከተደረገዉ የድርጅቱ ሪፎርም አንፃር የፓርቲዉን አደረጃጀት እስከ ታችኛዉ እርከን ድረስ የማደራጀት ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባዉን አጠናቋል፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም

አዲስ አበባ፥ ሸዋ፥ ኢትዮጵያ

LEAVE A REPLY