ኬንያዊ ጋዜጠኛ ከእስር እንዲፈታ ጠቅላይ ዐቃብ ሕግ አዘዘ

ኬንያዊ ጋዜጠኛ ከእስር እንዲፈታ ጠቅላይ ዐቃብ ሕግ አዘዘ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኬኒያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ መስጠቱ ተሰማ።

ያሲን ጁም ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል አንዱ ተጠርጣሪ እንደነበር ይታወሳል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ነሐሴ 1 በዋለው ችሎት ያሲን ጁማን ጨምሮ የ11 ሰዎች የዋስትና መብት ተከብሮላቸው በዋስ እንዲወጡ ብይን ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ ፖሊስ ያሲን ጁማን በሌላ የወንጀል ደርጊት ጠርጥሬዋለሁ ማለቱን ተከትሎ ጋዜጠኛው በእስር ለመቆየት ተገዷል።
ያሲን ጁም በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ  በኮሮናቫይረስ መያዙን ፖሊስ ባለፈው ሳምንት መግለጹ አይዘነጋም።
የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ ከድር ቡሎ፤ ያሲን በኮቪድ-19 በመያዙ በኢትዮጵያ የሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ ጋዜጠኛው ተለይቶ የሚቆይበት ቦታ ሲያዘጋጅ ከእስር እንደሚወጣ ይፋ አድርገዋል።
ያሲን ጁማ ከእስር እንዲለቀቅ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

LEAVE A REPLY