በኦሮሚያ የጸጥታ ኃይሎች ያደረሱትን የሰው ነፍስ ማጥፋት ኢሰመኮ በእጅጉ ኮነነ

በኦሮሚያ የጸጥታ ኃይሎች ያደረሱትን የሰው ነፍስ ማጥፋት ኢሰመኮ በእጅጉ ኮነነ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ለተቃውሞ በተጠሩ ሰልፎች ምክንያት የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን በእጅጉ የኮነነው የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ አሳሰበ።

በአሳሳ፣ አሰቦት፣ አወዳይ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጭሮ፣ ደንገጎ፣ ድሬ ጠያራ፣ ዶዶላ፣ ገለምሶ፣ ጊኒር፣ ሃሮማያ፣ ሂርና እና ሻሸመኔ ባሉ ከተሞች የሰዎች ሕይወት ማለፉን የሚያረጋግጥ መረጃ እንዳገኘ በዶክተር ዳንኤል በቀለ የሚመራው ኢሰመኮ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች (እነ ጃዋር) እንዲለቀቁ በተጠራ የተቃውሞ ሰልፍ የሰው ሕይወት ማለፉን የጠቆመው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን፤ “የመንግሥት አካላት የዜጎችን በሰላማዊ መልኩ ተቃውሞ የማሰማት መብት ማረጋገጥ እንዳለባቸው እና ሕግ የማስከበር ሥራም ተመጣጣኝነት እንዲጠብቅ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው” ገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል በዚህ ዓመት የተከሰቱ አሳዛኝ ግድያዎች ከፈጠሩት ሰቆቃ አሁንም ፈጽሞ አላገገመም፡፡ በመሆኑም እነዚህ ከፍተኛ የመብት ጥሰት አዝማሚያዎች እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው አይገባም ሲል መግለጫ ያወጣው ኢሰመኮ፤ የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ በሚዲያዎችና በሪፖርቶች የተለያየ መረጃ እየወጣ ቢህንም፣ ስለደረሰው ሞትና ጉዳት መጠን ለማረጋገጥ ከነዋሪዎች፣ አይን እማኞች፣ ሆስፒታሎችና አስተዳር አካላት ትክክለኛ መረጃ እየሰበሰብኩ ነው ብሏል።
 የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ጉዳዩን ለማጣራት በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀምሩም  የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ከወዲሁ መልእክት አስተላልፏል።

LEAVE A REPLY