ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሻሸመኔ ከተማ የጸጥታ ሥራን በማከወን ላይ በነበሩ ጸጥታ አስከባሪዎች ላይ ቦምብ የወረወረ የኦነግ ሸኔ አባል ላይ እርምጃ እንደተወሰደበት የከተማዋ ፖሊስ አስታወቀ።
ዛሬ ሀሙስ ነሐሴ ከጠዋቱ አንድ ሰዐት ተኩል አካባቢ በሻሸመኔ ከተማ 01 ወይም አዋሾ ቀበሌ አካባቢ የጸጥታ ሀይሎች አካባቢያዊ ዳሳሳ ቅኝት ሲያደርጉ ነው ቦንቡ የተወረወረባቸው።
የሰላም አስከባሪዎቹ ላይ ከድር ቱሌ የተባለ ግለሰብ የእጅ ቦምብ ወርውሮ ሊያመልጥ ሲል እርምጃ የተወሰደበት በመሆኑ የተጠርጣሪው ህይወትም ማለፉ ታውቋል።
የኦነግ ሸኔ አባል ነው የተባለው ግለሰብ ቦምብ ከወረወረባቸው የጸጥታ ሀይሎች መካከል በአንዱ ላይ ጉዳት በመድረሱ በመልክ ኦዳ ሆስፒታል ክትትል እየተደረገለት መሆኑም ተገልጿል።
የሻሸመኔ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ከተጠርጣሪው እጅ ላይ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ መገኘቱን ጠቁሞ፤ ከድር ቱሌ የተባለው ይህ ተጠርጣሪ መታወቂያው የአርሲ ዞን ሸርካ ወረዳ ነዋሪ እንደሆነ የሚያሳይ እንደሆነና ሁለት ሞባይል፣ በዛ ያለ ገንዘብ እና ትጥቅ መያዣ ቀበቶ ይዞ እንደነበርም ይፋ አድርጓል።
የከተማው ፖሊስ መምሪያ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በጥምረት በከተማዋ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝና ሻሸመኔ አሁን ላይ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን የፖሊስ ኮሚሽኑ አረጋግጧል።