ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወጪ አስቀድሞ ከታሰበው በእጥፍ ያህል ገንዘብ እንደሚያስወጣ ተነገረ።
የግድቡ ግንባታ ሲጀመር 78.3 ቢሊየን ብር ይፈጃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 121.5 ቢሊየን ብር ወጪ እንደተደረገበት ነው የታወቀው።
ግድቡ አሁን ላይ በተያዘለት ፕሮግራም 2015 ዓ.ም ሲጠናቀቅ አጠቃላይ ወጪው 160 ቢሊየን ብር ይሆናል ተብሎ መሰላቱ ይፋ ተደርጓል።
ግድቡ አሁን ያለበትን የግንባታ ሁኔታ በተመለከተ የግድቡ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የግድቡ ሲቪል ሥራ 88 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ደግሞ 46 በመቶ ላይ መድረሱን የተናገሩት የግድቡ ሥራ አስኪያጅ አጠቃላይ ግንባታው 75 በመቶ እንደደረሰ ጠቁመው፤ በ2013ዓ/ም የግድቡ ግንባታ ላይ 2 ትልልቅ ሥራዎች እንደሚጠበቅ ከመግለጻቸው ባሻገር፤ የግድቡን የማዕከለኛ ከፍታ፤ ከ560 ሜትር ወደ 595 ሜትር ከፍ ማድረግ፣ ሁለተኛ ደግሞ የሀይል ማመንጨት ሙከራ እንደሚከናወኑ አብራርተዋል።
የግድቡ የኤሌክትሮ መካኒካልም ሆነ የሲቪል ሥራ በመጪው ዓመት በተያዘላቸው እቅድ መሰረት እንዲሠሩ ከፍተኛ ርብርብ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡